የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ ሀላፊነታችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ ሀላፊነታችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን
ነሀሴ 7/2013 (ኢዜአ) ቀደምት የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ የተወጡትን ሀላፊነት ለመድገም ዝግጁ መሆናቸውን የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ገለፁ።
ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤም ኢትዮጵያዊያን አገር ለማፍረስ ለተነሱ ሃይሎች ዓላማቸው እንደማይሳካ ከማሳየት ባሻገር የኢትዮጵያን ትንሣኤና ብልፅግና እንዲያስቀጥሉ ጠይቀዋል።
በአዲስ አበባ ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ስር ከሚገኙት አራት ትያትር ቤቶች ተውጣጥተው ወደ ግንባርና ማሰልጠኛዎች ለሚጓዙ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ሽኝት ተደርጓል።
የቢሮ ኃላፊዋ ወይዘሮ ፋኢዛ መሀመድ ኪነ-ጥበብ አገር ፈተና ላይ በወደቀችባቸው ጊዜያት ሁሉ ጦር ግንባር ድረስ በመሄድ የማበረታታት ሚናዋን ስትወጣ መቆየቷን አውስተዋል።
አሸኛኘት የተደረገላቸው የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ሕዝብ በትግሉ ያገኘውን ነፃነት ለመቀማት አፍራሽ ተልዕኮ አንግቦ እየተንቀሳቀሰ ካለው አሸባሪ ቡድን ጋር የሚደረገውን ትግል እንዲያግዙም አስገንዝበዋል።
ኪነ-ጥበብ አገር ለማዳን የሚጠበቅባትን መወጣት አለባት በማለት አሻራቸውን በታሪክ ለማስመዝገብ በሚሰማሩባቸው የማሰልጠኛ ተቋማትና የጦር ግንባሮች አገራዊ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡም እምነታቸውን ገልፀዋል።
ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው በአገር ውስጥና በውጭ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የሚተጉ አካላት ዓላማቸው እንዳይሳካ ከማድረግ በተጨማሪ የኢትዮጵያን ትንሳኤና ብልፅግናዋን ለማረጋገጥ መትጋት እንደሚገባም አሳስበዋል።
ትናንት ኢትዮጵያን ያጀገናትና ውጤታማ ያደረጋት አብሮነትና አንድነት ዛሬም በዚህ ትውልድ እየተደገመ ነው፤ አሁንም ታሪክን በወርቅ ብዕር እየፃፍን እንቀጥላለን ብለዋል።
ኪነ-ጥበብ ታነቃቃለች፣ ታጀግናለች፣ አርበኛም ታደርጋለች ይህንንም በታሪክ አይተናል ያሉት ምክትል ከንቲባዋ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ጀግኖችን ይበልጥ ለማጀገንና የኢትዮጵያን ድል አድራጊነት ለማብሰር ወደ ግንባር ለመሄድ በመወሰናቸው ክብርና ምስጋና እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
ወደ ማሰልጠኛ ተቋማትና ወደ ግንባር ለመዝመት ከአዲስ አበባ ትያትርና ባህል አዳራሽ፣ ከአገር ፍቅር፣ ከራስና ከሕፃናትና ወጣቶች ቲያትር ቤቶች የተውጣጡት ባለሙያዎች ስላደረጉት ዝግጅት የአዲስ አበባ ትያትርና ባህል አዳራሽ ስራ አስኪያጅ አርቲስት ካሳዬ ገበየሁ አብራርቷል።
በኢትዮጵያ ማሲንቆና ክራር ከአገር ጋር ያላቸውን ቁርኝት በማውሳት ኪነ-ጥበብ አገር ችግሮች በገጠሟት ጊዜ አቤት ብላ ሚናዋን የምትወጣ መሆኗን ገልጿል።
የኪነ-ጥበብ ባሙያዎቹ የኢትዮጵያን አንድነት ለማስቀጠል የቀደመ ሚናቸውን ለመወጣት የተለያዩ የጥበብ ስራዎችን በማሰናዳት ወደ ማሰልጠኛ ተቋማትና ጦር ግንባር ለመዝመት ተዘጋጅተዋል ብሏል።
የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎቹም ቀደምት የሙያ አጋሮቻቸው ለአገር አንድነት በማስጠበቅና ዘማቾችን በማነቃቃት ያበረከቱትን አስተዋፅኦ ለመድገም መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
አገር የምትገነባው በሁሉም ጥረት ነውና ሁሉም በየዘርፉ በእኔነት ስሜት ሊሰራ እንደሚገባም የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎቹ ተናግረዋል።