ቀጥታ፡

ዳያስፖራው ከመንግሥት ጎን በመሆን ለአገሩ ሁለንተናዊ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 07፣ 2013 (ኢዜአ) ዳያስፖራው ከመንግሥት ጎን በመሆን ለአገሩ ሁለንተናዊ ድጋፍ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ዳያሥፖራ ማህበራት ጥምረት ጥሪ አቀረበ፡፡

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበራት ጥምረት በወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ ላይ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ 

በመግለጫውም ኢትዮጵያ ከተጋረጠባት ችግር በድል አድራጊነት እንድትሻገር አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍና እገዛ የሚያደርጉ መሆኑን የዳያስፖራ ተወካዮች ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዳያሥፖራ ማህበራት ጥምረት ሰብሳቢ ወይዘሮ ሶስና ወጋየሁ እንዳሉትም ዳያሥፖራው ሀገሩ የምትጠብቅበትን ሁሉ ለመወጣት ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የገጠማትን ችግር ለመፍታት በሚደረገው ጥረትም ዳያሥፖራው ከመንግስት ጎን በመሆን የራሱን አስተዋጽኦ ማድረግ ላይ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ያለው ወቅታዊ ችግር ተፈቶ ህዝቡ በሙሉ አቅሙ ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞር የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ጥምረት ከመቼውም ጊዜ በላይ ከመንግስት ጎን መሆኑን ጠቅሰው፤ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉም በልማቱና በሌሎች ተግባራት አገራቸውን ያግዛሉ ብለዋል።

ዳያሥፖራው አገሩን በገንዘብ ለመደገፍም በመንግስት እውቅና ባላቸው አካውንቶች ብቻ መሆን እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ 

የኦሮሚያ ዳያሥፖራ ማህበር ዋና ጸሐፊ አቶ ሞሣ ሼኮ፤ ኢትዮጵያ ካለችበት ፈተና እንዳትወጣ የሚሰሩ አካላትን ሁሉ ለመመከት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በትላልቅ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም ጭምር በመቅረብ ስለ ኢትዮጵያ ሰላም፣ ጸጥታና አንድነት በመሞገት የተሳሳተ አመለካከትን በማረም ትክክለኛውን አቅጣጫ ማስያዝ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ዳያሥፖራው በህዳሴ ግድቡ ዙሪያም ከግብጽና አጋሮቿ የሚወጡ የሀሰት ፕሮፓጋንዳዎችን ከመመከት አንጻር አዎንታዊ ስራ በመስራት ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዳያሥፖራ ማህበራት ጥምረት በስሩ 12 ማህበራትን ያቀፈ ሲሆን ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ዕድገት መሳካት በመስራት ላይ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም