ቀጥታ፡

የትግራይ ወጣቶች ለአሸባሪው ህወሃት የጥፋት መሳሪያ ከመሆን እንዲታቀቡ የክልሉ ተወላጆች ጥሪ አቀረቡ

ነሀሴ 7/2013 (ኢዜአ)  የትግራይ ክልል ወጣቶች ህይወታቸውን አደጋ ላይ ከመጣልና የአሸባሪው ህወሃት የጥፋት መሳሪያ ከመሆን እንዲታቀቡ የክልሉ ተወላጆች ጥሪ አቀረቡ።
በአዲሰ አበባ በንግድ ስራ የሚተዳደረውና የማህበረሰብ አንቂ የሆነው ወጣት ሰለሞን ወልደገሪማ፤ ህወሃት ኢትዮጵያን ሲያስተዳድር የኖረው በደልና አሻጥሮችን እየሰራ መሆኑን ይናገራል።   

የህወሃት ቡድን ለወጣቱ የተሻለ የስራ እድል ከመፍጠር ይልቅ የጥላቻ ትርክቶችን በመንዛት እርስ በእርስ መከፋፈል እንዲኖር ሲሰራ መቆየቱንም አስታውሷል።

አሁን ደግሞ በሽብር ተግባር ላይ ተጠምዶ ከተለያዩ አፍራሽ ሃይሎች ጋር በመሆን ኢትዮጵያን ለመበታተን እየሰራ መሆኑን ተናግሯል።

አሸባሪው ህወሃት ወትሮም ቢሆን ከራሱና በጥቅም ከተሳሰራቸው አካላት ውጭ ለህዝብ ግድ የማይሰጠው ቡድን መሆኑን ሁሉም ይገነዘባል ብሏል ሰለሞን።

የትግራይን ህዝብ በተለያዩ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ እያኖረ ለራሱና ለዓላማው አስፈፃሚዎች ብቻ ሲፍጨረጨር የኖረ አገር ከፋፋይ ሃይል መሆኑን አስረድቷል።

የህወሃት አሸባሪ ቡድን በኢትዮጵያ ህዝቦች ትግል ተወግዶ ወደ ትግራይ ሂዶ ከመሸገ በኋላ የክልሉ ህዝብ ተቆርቋሪ መስሎ ለመቅረብ ብዙ ጥረት አድርጓል ብሏል።

አሸባሪ ቡድኑ የአገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝን አጥቅቶ ከባድ የአገር ክህደት ወንጀል መፈፀሙ ይታወቃል።

ከዚህ የአገር ክህደቱ ጋር የትግራይ ህፃናትና ወጣቶች ለውጊያ በግድ እንዲሰለፉ በማድረግ በወንጀሉ ገፍቶበታል ብሏል።

የህወሃት የሽብር ቡድን የራሱን ቤተሰቦችና ልጆች በተለያዩ አገራት እያኖረና እያስተማረ የትግራይ ደሃ ቤተሰብ ልጆችን ለጦርነት እየማገዳቸው በመሆኑ ሊቃወሙት ይገባል ብሏል።

በማህበራዊ ሚዲያ የሚያሰራጨውን የውሸት ፕሮፖጋንዳ ባለመቀበል የትግራይ ወጣቶች የህወሃትን የሽብር ቡድን "በቃህ" ሊሉት ይገባል ብሏል።

የትግራይ ወጣቶች የኢትዮጵያ መንግስት ያቀረበውን አገር የማዳን ጥሪ በመቀበል ድጋፋቸውን እንዲያሳዩም ወጣት ሰለሞን ጥሪ አቅርቧል።

በአዲስ አበባ የሚኖሩት የትግራይ ክልል ተወላጅ የሆኑት አቶ ዮሃንስ ጎይቶም በበኩላቸው የሽብር ቡድኑን የትግራይ ህዝብ "ከጀርባው የሚያወርድበት ጊዜ አሁን ነው" ብለዋል።

የህወሃት አሸባሪ ቡድን ከራሱ ጥቅም ውጭ ለህፃናት፣ ሴቶች፣ ወጣቶች አረጋዊያን እንዲሁም ለህዝብ ደንታ የሌለው የጨካኞች ስብስብ መሆኑን ደግሞ አርቲስት ሰናይት ሃይለማሪያም ገልፃለች።

በመሆኑም የትግራይ ወጣቶች የሽብር ቡድኑን እኩይ ዓላማ በመቃወም ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ወደ ተጀመረው ዘመቻ መቀላቀል አለባቸው ብላለች።

ኢትዮጵያውያን አገር ለማፍረስ ከውስጥና ከውጭ ግንባር ፈጥረው የሚሰሩ አካላትን በጋራ ሆነው መመከት እንዳለባቸው ገልፃለች።

በቀደምት አባቶችና እናቶች ክብሯና ሉአላዊነቷ ተከብሮ የቆየችው ኢትዮጵያ ህልውናዋ ተጠብቆ እንዲቀጥል የሁላችንም ሃላፊነት ነው ብለዋል አስተያየት ሰጭዎቹ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም