የህወሓትን አሸባሪ ቡድን ለመመከት በሚደረገው ጥረት የበኩላችንን ሃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ ነን - ኢዜአ አማርኛ
የህወሓትን አሸባሪ ቡድን ለመመከት በሚደረገው ጥረት የበኩላችንን ሃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ ነን
አዲስ አበባ፤ ነሀሴ 06 ቀን 2013 (ኢዜአ) የህወሃትን አሸባሪ ቡድን ለመመከት በሚደረገው ጥረት የበኩላችንን ሃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን የተለያዩ የሲቪክ ማህበራት ገለፁ። ማህበራቱ አሸባሪው የህወሃት የሽብር ቡድን በአፋር ክልል በሕጸናት፣ ሴቶችና አረጋውያን ላይ የፈፀመው ግዲያ በፅኑ አውግዘዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አሸባሪው የህወሃት ቡድን በኢትዮጵያ ላይ የደቀነውን የህልውና ስጋት ዜጎች በጋራ እንዲመክቱ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።
በመግለጫውም ሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ የአገር ሉአላዊነትን ለማስጠበቅ አሸባሪውን ሃይል እንዲመክት አሳስቧል።
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር፣ የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን አገርን የማዳን ጥሪውን በመቀበል የበኩላቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሐንስ በንቲ፣ በመላ አገሪቷ ያሉ መምህራን መንግስት ያቀረበውን አገር የማዳን ጥሪ ተቀብለው የአሸባሪውን ህወሃት አገር የማፍረስ ዓላማ እንደሚመክቱ አረጋግጠዋል።
አገር የማዳን ጥሪው የሁሉም ኢትዮጵያዊ የዜግነት ሃላፊነት በመሆኑ ተማሪዎች፣ መምህራን እና ሌሎችም በአንድነት በመቆም የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
መንግስት የወሰደውን የተናጠል ተኩስ አቁም አሸባሪ ቡድኑ አንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ በዜጎች ላይ ጥቃት እየፈፀመ መሆኑን ገልጸዋል።
ቡድኑ በአፋር ክልል በህፃናት ላይ ያደረሰውን ዘግናኝ ጭፍጨፋ ዶክተ ዮሐንስ አውግዘዋል።
የሴቶች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አስካለ ለማ በበኩላቸው የህወሃት አሸባሪ ቡድን ለ27 አመታት ኢትዮጵያን በሚያስተዳድርበት ወቅት በኢትዮጵያ ወጣቶች፣ ሴቶች እና ህዝቦች ላይ ግፍ ሲፈፅም እንደነበ ገልጸዋል።
የሽብር ቡድኑ አሁንም አገር የማፍረስ ዓላማ ይዞ እየሰራ መሆኑን ገልጸው በተባበረ ክንድ መመከት ይገባል ብለዋል።
ለአገር ሉአላዊነት በመዋጋት፣ ስንቅ በማዘጋጀት፣ ደም በመለገስ እና በሌሎችም ሴቶች የላቀ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቷ በንግግራቸው “ትናንት በአያት ቅደመ አያቶቻችን በጠላት ያልተደፈረች አገር ዛሬ በአሸባሪ ቡደን እንዲትፈርስ አንፈቅደም” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴረሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ፅገረዳ ዘውዱ፤ የአሸባሪው ውጊያ በጦር ሜዳ ብቻ የሚካሄድ ባለመሆኑ ወተለይ ወጣቶች በሁሉም መስክ ለመመከት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ህብረተሰቡ በማህበራዊ ሚዲያ በሚሰራጩ የሃሰተኛ መረጃዎች እንዳይደናገር ወጣቱ ትክክለኛ መረጃ በማድረስ የድርሻውን መወጣት አለበት ብለዋል።
የህወሃት አሸባሪ ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ "ሲኦልም ቢሆን እንገባለን" በማለት ሌት ከቀን እየሰራ መሆኑ ይታወቃል።