ቀጥታ፡

ልጆቻቸውን እያጀገኑ፤ ለሀገር መርቀው የሚልኩ ወላጆች ባሉባት ሀገር ኢትዮጵያ አትፈርስም!

ሚዛን፤ ነሐሴ 6ቀን 2013(ኢዜአ)''ልጆቻቸውን እያጀገኑ ለሀገር መስዋዕትነት እንዲከፍሉ መርቀው የሚልኩ ወላጆች ባሉባት ሀገር ኢትዮጵያ አትፈርስም'' አሉ የቀድሞ ብሔራዊ ወታደር።
ብሔራዊ ወታደር ጥላሁን ገብሬ የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪ  ናቸው፤ ዘንድሮ 55 ዓመት ሞልቷቸዋል።

በቀድሞ የካፋ ክፍለ ሀገር ጅማ ከተማ የተወለዱና በ1977 ብሔራዊ ውትድርና አገልግሎትን ተቀላቀሉ።

በወቅቱ ከሚማሩበት ትምህርት ቤት ደብተራቸውን ለጓደኞቻቸው ሰጥተው ከመሄድ ውጭ ቤተሰባቸውን ለመሰናበት እንኳን ዕድል አላገኙም።

በውትድርና ሰልጥነው ሰባተኛ ክፍለ ጦርን ተቀላቀለው ኤርትራ ውስጥ ሲዋጉ ያቆሰላቸው ጥይት ዛሬም በሰውነታቸው ይዘው እንደሚኖሩ ነው ለኢዜአ  የተናገሩት።

’’መስዋዕትነቴ የኢትዮጵያን አንድነትና ክብሯን ለመጠበቅ ነው''ይላሉ በኩራት።

ዛሬ ኢትዮጵያን የገጠማት ጦርነት እሳቸው ከገጠማቸው የተለየ መሆኑንም ብሔራዊ ወታደር ጥላሁን ይገልጻሉ።

''ልጆቻቸውን እያጀገኑ ለሀገር መስዋዕትነት እንዲከፍሉ መርቀው የሚልኩ ወላጆች በማየቴ ተደስቻለሁ። እነዚህ መበረታታት አለባቸው።''

''የደረሰ ልጅ ስለሌለኝ እንጂ፤ለመላክ ፍላጎት ነበረኝ''በማለትም ይቆጫሉ።

''ጦርነቱ የሕዝብ ደጀንነት ያለው ነውና በድል ይሻገራል''ሲሉም  ያክላሉ።

’’እኔም በግሌ ወደ ቦታው ሂዶ ለመዋጋት ሰውነቴ ላይ ያለው ቁስል ስለማያስችለኝ ባለሁበት ሁኜ ሰርጎ ገቦችን በመከታተል የአካባቢ ሰላም እጠብቃለሁ’’ ብለዋል።

በተጨማሪም የአንድ ወር  ደመወዛቸውን ለሀገር መከላከያ ሠራዊት መስጠታቸውን አስታውቀዋል።

ብሔራዊ ወታደር ጥላሁን ገብሬ  ''ጦርነቱ ሀገርን ከተደቀነባት አደጋ ለማውጣት በተባበረ ክንድና በአንድነት መንፈስ የሚደረግ በመሆኑ ወያኔ የመቀበሪያ ጊዜዋ መድረሱን ያሳያል፤ ድል የኢትዮጵያ ይሆናል'' በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ንጉሴ ሳፕለት፤ ሀገር ለማዳን የሚካሄደው ዘመቻ በገንዘብና ስንቅ  ከመደገፍ ባሻገር ሀገራዊውን ጥሪ በመቀበል ለመዝመት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

 አቶ ንጉሴ፤አካባቢያቸውን በንቃት በመጠበቅ የአሸባሪውን ተልዕኮ ለማስፈጸም የሚንቀሳቀሱ አካላትን በማጋለጥም ግዴታቸውን ለመወጣት ዝግጁ  ናቸው።

ወይዘሮ ጨነቁ በፍቃዱ፤ "ነፍሰ ጡርን ጭምር ለጦር ያሰለፈና ሀገርን ለመበተን የቃጣውን አረመኔ ቡድን በመደምሰስ ሀገራችንን ለመታደግ እስከ ግንባር ድረስ ለመሄድ ዝግጁ ነኝ"ብለዋል።

የመከላከያ ሰራዊት አባል በመሆን ሀገሩን ለማገልገል ዝግጁ መሆኑን  ያስታወቀው ደግሞ ወጣት ምስጋናው ባምላኩ ነው።

እኛ ኢትዮጵያዊያን  በቃን ብለን ከተነሳን ከፊታችን የሚቆም ምንም ዓይነት ሃይል እንደሌላ ታሪክ ምስክር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም