የኢትዮጵያ ወጣቶች በሕልውና ትግሉ ውስጥ በግንባር ቀደምነት ተሳትፎ እያደረጉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ወጣቶች በሕልውና ትግሉ ውስጥ በግንባር ቀደምነት ተሳትፎ እያደረጉ ነው
ነሃሴ 5/2013 /ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ወጣቶች የአገሪቷንና የዓለም አቀፉን ማሕበረሰብ ነባራዊ ሁኔታ ተረድተው በሕልውና ትግሉ ውስጥ በግንባር ቀደምነት ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸውን የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ገለጸ።
የትግራይ ወጣቶችም የአሸባሪውን ሴራ ወደ ጎን ትተው ኢትዮጵያን ለማዳን መንቀሳቀስ እንዳለባቸውም አስታውቋል።
የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ዙሪያ የኢትዮጵያ ወጣቶች ሚናን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጠው የሊጉ ዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊና የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ወጣት አክሊሉ ታደሰ እንደተናገረው፤ አሻባሪው ሕወሃት ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ቆይታው የኢትዮጵያ ወጣቶች የጋራ ርዕይ እንዳይኖራቸው አድርጓል።
አሸባሪው ሕወሓት በህዝብ ላይ የፈጸመው ግፍ አልበቃ ብሎት በመጨረሻ በመከላከያ ሰራዊት ላይ የሀገር ክህደት መፈጸሙን አስታውሷል።
አሻባሪው በእኩይ ድርጊቱ መቀጠሉንና ወጣቶችም ቡድኑን በግምባር ቀደምነት እየተፋለሙ እንደሚገኙም አመልክቷል።
በእስካ አሁኑ ሂደት ወጣቶች መንግስት ያደረገውን ጥሪ ተቀብለው በሙሉ አቅማቸውና በሚችሉት ሁሉ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ነው ጠቅሷል።
በቀጣይም የኢትዮጵያ ወጣቶች የሀገራቸውንና የዓለም ዓቀፉን ማሕበረሰብ ነባራዊ ሁኔታ በአግባቡ ተረድተው የተደቀነውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ መታገል እንዳለባቸው ነው የተናገረው።
ከዚህ ባለፈም ወጣቶች የሕወሃት አሸባሪ ቡድን ከሚነዛው ፕሮፓጋንዳ እራሳቸውን መጠበቅና ሌሎችንም ማንቃት እንዳለባቸው ጠቁሟል።
እንደ ወጣት አክሊሉ ገለጻ፤ ወጣቶች በኢትዮጵያ ላይ የውክልና ጦርነት መከፈቱን ተረድተው የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ሊወጡ ይገባል።
ከዚህ ጎን ለጎን የአሻባሪው ቡድን እኩይ ሴራ በርካታ የኢትዮጵያ አካባቢዎች እንዳይረብሽ፤ "ወጣቶች የአካባቢያቸውን ሰላም በንቃት መጠበቅ አለባቸውም" ብሏል።
የአገሪቷ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እክል እንዳይገጥመው፤ የኢትዮጵያ ወጣቶች ከበፊት በተሻለ መልኩ እንዲንቀሳቀሱም ጥሪ አቅርቧል።
ሊጉ በሚቀጥሉት ሶስት ሳምንታትም ወጣቶችን የማንቃት፣ በማሕበራዊና በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘርፍ በስፋት እንዲሳተፉ የማድረግ ስራ እንደሚሰራም ጠቁሟል።
ወጣት አክሊሉ እንደገለጸው፤ የትግራይ ወጣቶች የአሸባሪውን ሴራ መረዳትና መታገል አለባቸው።
የብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ከ10 ሚሊዮን በላይ የሆኑ አባላትና ደጋፊዎች ያሉት መሆኑን ወጣት አክሊሉ ገልጿል።