አሸባሪው ህወሃት የፈጸመውን ወረራ ለመመከት በጋራ እንሰለፋለን…በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ህወሃት የፈጸመውን ወረራ ለመመከት በጋራ እንሰለፋለን…በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች
ባህርዳር፤ነሃሴ6/2013(ኢዜአ) በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሸባሪው ህወሃት የፈጸመውን ወረራ ለመመከት እንደ ህዝብ በአንድነትና በጽናት ወደ ግንባር በመዝመት ለመፋለም ቆርጠው ተነስተዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አሸባሪው ቡድን በሃገር ላይ አደጋ ለመፍጠር እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይል ንቅናቄ/አዴሃን/ ሊቀመንበር አቶ ተስፋሁን አለምነህ በጋዜጣዊ መግለጫው እንዳሉት አሸባሪው ህወሃት ቀደም ሲል የፈጸመው በደል ሳያንሰው ዳግም ወረራ በአማራና አፋር ክልሎች ፈጽሟል።
ይህ የእብሪት ቡድን በተለያዩ አካባቢዎች እየፈጸመ ያለው ወረራ ኢትዮጵያን ወደ ማያባራ ብጥብጥ፣ ደም መፋሰስና እልቂት ለማስገባት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
በሚደርስባቸው አካባቢዎችም ሴቶችን በመድፈር፣ ንጹሃንን በመግደልና አካል በማጉደል ከሚፈጽመው በላይ የስነ ልቦና ጫና እያደረሰ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
ቡድኑ ባካሄደው ወረራም እስከ አሁን ድረስ ከ300ሺህ በላይ ህዝብ ከቀየው ተፈናቅሎ በአስቸጋሪው የክረምት ወቅት ለእንግልት መዳረጉን አብራርተዋል።
“በተለይም በአፋር ክልል በጊዜያዊ መጠለያ የነበሩ ከ270 በላይ ሴቶች፣ ህጻናት፣ አረጋውያንና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን በጅምላ መጨፍጨፉ የሽብር ጥጉን ያረጋገጠበት ነው” ብለዋል።
ወረራውን ለመቀልበስ ፈጣን ምላሽ ለሰጡ የአማራ ልዩ ሃይል፣ ሚሊሻ፣ የመከላከያ ሰራዊትና የሌሎች ክልሎች የጸጥታ አባላት ቡድኑን በግንባር በመፋለም ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
አማራን በማጥፋት ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የሚቋምጠው ቡድን መላው የኢትዮጵያ ህዝብም በተባበረ ክንድ ለመፋለም ያሳየው ተነሳሽነነት የሚበረታታ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ነሃሴ 4/2013 ዓ.ም መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔውን ማንሳቱ በተባበረ ክንድ አሸባሪውን ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቅበር የሚያስችል መሆኑንም በመግለጫው አመልክተዋል።
ለዚህ ፍትሃዊና የህልውና ትግል መላ የድርጅታቸው አባላት ሰልጥነው ወደ ግንባር በመትመም የሚጠበቅባቸውን አገራዊ ሃላፊነት ለመወጣት የጀመሩትን ተግባር አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ/አብን/ የውጭ ጉዳይና አለም አቀፍ ጉዳዮች ሃላፊ ዶክተር ቴዎድሮስ ሃይለማርያም በበኩላቸው አሁን ላይ አሸባሪው ቡድን በመላው የአማራ ህዝብ ህልውና ላይ አደጋ ፈጥሯል።
“በክልላችን ላይ የፈጸመው ወረራና እያደረሰ ያለው ጉዳት የታሪክ ዝቃጭነቱን ያረጋገጠ ድርጊት ሆኖ ሲወሳ የሚኖር ነው” ያሉት ዶክተር ቴዎድሮስ፤ "ይህን እኩይ ሴራ መመከት የሁሉም አማራ መሆን አለበት” ብለዋል።
በመሆኑም መላ የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች አቅም ያላቸው ሰልጥነው ወደ ግንባር በመዝመት፣ አቅም የሌላቸው በገንዘብና በእውቀታቸው በሚችሉት ሁሉ ትግሉን በሙሉ ልብ ደግፈው ተሳታፊ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።
“የአማራ ህዝብ በአሁኑ ወቅት በአሸባሪው ቡድንና ተባባሪዎቹ ወረራና ከበባ ተፈጽሞበታል” ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብርሃም አለኸኝ ናቸው።
“በሰሜን ወሎ ዞን ያካሄደውን ወረራ በአሁኑ ወቅት ወደ ደቡብ ጎንደር በማስፋት በዜጎቻችን ላይ ሰቆቃ እየፈጸመ በመሆኑ ሁሉም የክልላችን ህዝብ ባጭር ጊዜ ቡድኑን ለመደምሰስ መነሳት አለበት” ብለዋል።
ቡድኑ በየደረሰባቸው አካባቢዎች "ዜጎቻችን ለዘመናት ያፈሩትን ሃብትና ንብረት በመዝረፍ ወደ መቀሌ በመጫን ዳግም ዘራፊነቱን በገሃድ እየፈጸመ ይገኛል" ሲሉም ገልጸዋል።
“በአማራ ክልል የምንቀሳቀስ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዛሬ በአንድነት መግለጫ መስጠት ያስፈለገውም በአገራችን ላይ የተቃጣውን የአሸባሪዎች ጥምረት በመመከት አስተሳሰባቸውን ለመቅበር በማሰብ ነው” ብለዋል።
ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ በሃሰተኛ ወሬ ሳይደናገር የሚመጣውን የጠላት ማዕበል በመደምሰስ የማይቀረውን ድል በጋራ ለማብሰር በአንድነት መሰለፍ ይግባናል ብለዋል።