''በአሸባሪው ህዋሃት በአገር ላይ የተከፈተብንን የውክልና ጦርነት ለመመከት ዜጎች በጋራ መቆም አለባቸው'' - ኢዜአ አማርኛ
''በአሸባሪው ህዋሃት በአገር ላይ የተከፈተብንን የውክልና ጦርነት ለመመከት ዜጎች በጋራ መቆም አለባቸው''

አዲስ አበባ፣ነሃሴ 06/2013 (ኢዜአ) ''በአሸባሪው ህዋሃት በአገር ላይ የተከፈተብንን የውክልና ጦርነት ለመመከትና የኢትዮጵያን ህልውና ለማስቀጠል ዜጎች በጋራ መቆም አለባቸው ሲሉ የታሪክ ምሁሩ ታዬ ቦጋለ ገለጹ።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት መምህር ታዬ፤ አሸባሪው የህወት ቡድን ከውጭ ጠላቶች ጋር በማበር ''ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እንገባለን'' ብሎ መነሳቱ ግልፅ የአገር ክህደት እየፈፀመ መሆኑን ገልጸዋል።
አሸባሪ ቡድኑ ከጅምሩ አንስቶ የተመሰረተው በጸረ - ኢትዮጵያ ሃይሎች መሆኑን ጠቅሰው ይህንኑ ዓላማውን ለማሳካት እየሰራ ነው ብለዋል።
ህወሃት ከተቋቋመበት የእኩይ ዓላማ በተቀራኒ የቆመውን ሁሉ ሲያጠፉና አገሪቷን ለ27 አመታት በሴራና የከፋፍለህ ግዛ ስልት ሲያስተዳድር የኖረ ቡድን መሆኑን ገልጸዋል።
ቡድኑ ከስልጣን ገለል ሲል ደግሞ ''እኔ ያልገዛኋት አገር ትፍረስ '' በሚል እሳቤ የጭካኔ ጥግ አሳይቷል ብለዋል መምህር ታዬ።
ለዚህም የጥቅምት 24 በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ የፈፀመውን ጥቃት ጨምሮ በርካታ የሽብርተኝነት ተግባራትን ፈፅሟል ብለዋል።
ቡድኑ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከሚደገፍበት ዋንኛ ምክንያቶች አንዱ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከምስራቁ አለም ጋር የፈጠረችውን ጠንካራ የኢኮኖሚ ትብብር ተከትሎ ጠንካራ አገር እንዳትሆን ለማዳከም መሆኑን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት 3 አመታት ብቻ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ሆናም ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላትን ትስስር ማጠናከሯና መጠነ ሰፊ ለውጦችን ማሳየቷ እንደ ስጋት እንድትታይ ያደረጋት እንደሆነም ጠቅሰዋል።
''የአፍሪካ አገራት ሁል ጊዜም ሸቀጥ ተቀባይ እንዲሆኑ በምዕራባዊያኑ ይሰራል'' ያሉት አቶ ታዬ፣ ከምስራቁ ዓለም ጋር በሚደረገው ፉክክር ውስጥ ኢትዮጵያን ማዳከም ዋና ዓላማቸው እንደሆነም ገልጸዋል።
''ኢትዮጵያ በተለያዩ ፈተናወች አልፋለች'' ያሉት የታሪክ ምሁሩ ይህን አስቸጋሪ ጊዜ ለማለፍ በአንድነት መቆም ይገባል ብለዋል።
ከአሸባሪው ቡድን በተጨማሪ በሱዳን በኩል የሚታየው ወረራና ሌሎችም ጫናዎች የበዙ መሆናቸውን በመጥቀስ ዜጎች በጋራ በመቆም ኢትዮጵያን ማዳን አለባቸው ብለዋል።