የአሸባሪው ህወሃት ኢሰብዓዊ የጭካኔ ድርጊቶች የቡድኑን ዓለም አቀፋዊ ወንጀለኛነት ያረጋገጡ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
የአሸባሪው ህወሃት ኢሰብዓዊ የጭካኔ ድርጊቶች የቡድኑን ዓለም አቀፋዊ ወንጀለኛነት ያረጋገጡ ናቸው
አዲስ አበባ ነሃሴ 06/2013(ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት ሀሰተኛ መረጃ በመንዛት ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የከፈተውን የመረጃ ጦርነት ለመመከት እውነታውን በማጋለጥ በሙያቸው ለአገር ሉዓላዊነት ዘብ እንደሚቆሙ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ገለፁ።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ የነበራቸው የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፣ የአሀዱ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት እና የዋልታ ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች በሙያቸው ለአገር ሉዓላዊነት ዘብ እንደሚቆሙ አረጋግጠዋል።
አሸባሪው ቡድን መንግስት የትግራይ አርሶ አደሮች ክረምቱን ለእርሻ ስራ እንዲያውሉ በማሰብ የወሰደውን የተናጠል ተኩስ አቁም እንደ ምቹ አጋጣሚ ተጠቅሞ የክልሉን ሕዝብ ለጦርነት መዳረጉን አንስተዋል።
መንግስት የሰጠውን የጥሞና ጊዜ ቡድኑ እንዴት ሲጠቀመው እንደነበር መላው ዓለም እንደሚገነዘበው የገለፁት ጋዜጠኞቹ በአፋርና በአማራ ክልሎች ጥቃት በመፈፀም በንፁሃን ላይ ጉዳት ማድረሱንም እንዲሁ።
የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋዜጠኛ ብስራት መለስ እና የዋልታ ቴሌቭዥን ጋዜጠኛ ስንታየሁ አባተ አሸባሪው ቡድን የተሰጠውን የጥሞና ጊዜ ለትግራይ ሕዝብ እፎይታ ሳይሰጥ ወደ ጦርነት ገብቷል ይላሉ።
የሽብር ቡድኑና የውጪ ሀይሎች በኢትዮጵያ ደካማ መንግስት እንዲኖር የጀመሩትን ዘመቻ የመገናኛ ብዙሃን መመከት የሚያስችሉ ስራዎች ላይ ትኩረት እድርገው መስራት እንደሚገባቸው አንስተዋል።
የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የመንግስትን ጥሪ ተቀብለው ማህበረሰቡን በማንቃት ኢትዮጵያዊያን ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድ ሆነው እንዲቆሙ የሚያስችሉ ስራዎችን መስራት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።
እውነታውን የኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ ዓለም አቀፉ ማኅበረስብ እንዲያውቀው ከአገር ውስጥ ቋንቋዎች በተጨማሪ በርካታ አድማጭና ተመልካች ባላቸው ቋንቋዎች ማጋለጥ እንደሚገባ ነው የተናገሩት።
የዋልታ ቴሌቭዥን ጋዜጠኛ ሜሮን መስፍን በበኩሏ አሸባሪው ህወሓት የጋረጠውን አገር የማፍረስ አደጋ ለማክሸፍ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ሕዝቡን ማንቃትን አጀንዳ ሊያደርጉ ይገባል ብላለች።
አሸባሪው የህወሓት ቡድን የከፈተውን የመረጃ ጦርነት እውነቱን በማጋለጥ ሃላፊነቷን እንደምትወጣ አረጋግጣለች።
ጋዜጠኞች በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ለሕዝብ የሚጠቅሙ ትክክለኛ መረጃዎችን ማቅረብ አለብን ያለው ደግሞ የአሀዱ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት ባልደረባው አሸናፊ እንዳለ ነው።
ጋዜጠኞቹ አሸባሪው ህወሓት ሀሰተኛ መረጃ በመንዛት ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የከፈተውን የመረጃ ጦርነት ለመመከት እውነቱን በማጋለጥ በሙያቸው ለአገር ሉዓላዊነት ዘብ እንደሚቆሙ አረጋግጠዋል።