ቱሪዝም ሰፊውን ህዝብ የሚያሳትፍ የልማት መስክ በመሆኑ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ቁልፍ ሚና ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
ቱሪዝም ሰፊውን ህዝብ የሚያሳትፍ የልማት መስክ በመሆኑ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ቁልፍ ሚና ይጫወታል
ነሐሴ 06 ቀን 2013 (ኢዜአ) ቱሪዝም ሰፊውን ህዝብ የሚያሳትፍ የልማት መስክ በመሆኑ በየደረጃው አሳታፊ የልማት ስኬት ለማስመዝገብ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ አስታወቁ።
ቱሪዝም ኢትዮጵያ ከኦዚ ሆስፒታሊቲ እና ቢዝነስ ግሩፕ ጋር የቱሪዝም ዘርፉን በተለያዩ መስኮች መደገፍ የሚያስችል የስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ የኢትዮጵያን የቱሪዝም ዘርፍ ትክክለኛ መረጃዎችን ለአለም አቀፉ ማኀበረሰብ ለማድረስ፣ የዘርፉን የኢንቨስተመንት ግንኙነት ለማሳደግ፣ የቱሪዝም መስተንግዶ ተግባርን ለማጠናከርና አመታዊ ፌስቲቫሎችን በኢትዮጵያ ከአለም አቀፍ ተቋማት ጋር ለማስተናገድ የሚያስችል ነው ተብሏል።
በስምምነት ሰነድ ፊርማ ወቅት ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ እንደተናገሩት፤ ቱሪዝም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የእድገት ምንጭ በመሆኑ መንግስት የአስር አመቱ የልማት መሪ ዕቅድ ዋና አካል ተደርጎ ተካቷል።
በዚህም ለዘመናት የተደበቀውን የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሃብት አውጥቶ ጥቅም ላይ ማዋል እና ለአለም ማስተዋወቅ ከፍተኛ ትኩርት ተሰጥቶበት እንደሚሰራ ነው ያመለከቱት።
በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመሩ የቱሪዝም ስራዎች ወደ ክልል መሸጋገራቸውን ጠቁመው፤ በቱሪዝም መሰረተ ልማት ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ቅድሚያ ተሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ባለፉት ጊዜያት ኮቪድ-19 ያመጣው ጉዳትና ከህግ ማስከበር ዘመቻው ጋር የተያያዙ ነገሮችን በመፍታት በዘርፉ ላይ ሰፊ ተግባራትን ለማከናወን አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል።
ቱሪዝም ሰፊውን ህዝብ የሚያሳትፍ የልማት መስክ በመሆኑ በየደረጃው አሳታፊ የልማት ስኬት ለማስመዝገብ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ቁልፍ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት።
የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዳይሬክትር አቶ ስለሺ ግርማ መንግስት በዘርፉ ከፍተኛ ማሻሻያዎችን በማድረግ በተለያዩ አካባቢዎች ገበታ ለሃገር በሚል የቱሪዝም መዳረሻዎችን እያለማ እንደሚገኝ አስታውሰዋል።
“በሌላ በኩል መንግስት ከግሉ ሴክተር ጋር በጋራ መስራትን የሴክተሩ ማሻሻያ አካል አድረጎ ወደ እንቅስቃሴ ገብቷል” ብለዋል።
“የግል ሴክተሩ በከፍተኛ ተነሳሽነት ኮንፍረንሶችን፣ ኤግዝቢሽኖችንና ልዩ ልዩ መርሐግብሮችን በማዘጋጀት ላይ ይገኛል፣ በተናጠል መስራቱ አይበቃም በሚልም በጋራ የሚሰሩበትን መድረክ ፈጥረዋል” ነው ያሉት።
በዚህም መንግስት ከግሉ ሴክተር ጋር ምን ልሰራ እችላለሁ በሚል ተቋማትን ማደራጀቱንም አመልክተው፤ ትክክለኛ መረጃ ለማድረስ፣ የዘርፉን የኢንቨስተመንት ግንኙነት ለማሳደግ፣ የቱሪዝም መስተንግዶ ተግባርን ለማጠናከርና አመታዊ ፌስቲቫሎችን ከግሉ ሴክተር ጋር መስራት መጀመሩን ተናግረዋል።
የዛሬው ስምምነትም እነዚህን እቅዶች ወደ ተግባር ለማስገባት የሚያስችል መሆኑን ነው የገለጹት ዳይሬክተሩ።
መንግስት የዘርፉን ኢንቨስትመንት ለማሳደግም በቱሪዘም መዳረሻዎች ላይ ባለሃብቶች እንዲሳተፉ ልዩ ልዩ ማበረታቻዎች ማድረጉን አስታውቀዋል።
የኦዝ ሆስፒታሊቲ እና ቢዝነስ ግሩፕ ኃላፊ አቶ ቁምነገር ተከተል ስምምነቱን ወደ ተግባር በመለወጥ እንደሚሰራ ተናግረው፤ ከተሞችን፣ መዳረሻዎችንና ያልታዩ የቱሪዝም መስህቦችን በማስተዋወቅ ከዘርፉ ሚገኘው ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።