አሸባሪው ህወሓት ላይ በሚወሰደው እርምጃ እስከ ህይወት መስዋዕትነት እንከፍላለን - የደሴ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ህወሓት ላይ በሚወሰደው እርምጃ እስከ ህይወት መስዋዕትነት እንከፍላለን - የደሴ ነዋሪዎች
ደሴ ፤ ነሐሴ 06/2013 (ኢዜአ) መንግስት ያስተላለፈውን ሀገራዊ ጥሪ በመደገፍ አሸባሪው ህወሓት ላይ በሚወስደው እርምጃ እስከ ህይወት መስዋዕትነት እንከፍላለን ሲሉ የደሴ ከተማ ነዋሪዎች አስታወቁ፡፡
ነዋሪዎቹ አሸባሪው ህወሓት ለቀጣይ ስጋት በማይሆን መልኩ ለመጨረሻ ጊዜ መደምሰስ እንደሚያስፈልግ ለኢዜአ ተናግረዋል።
በደሴ የመናፈሻ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ አየለ አህመድ ፤ የሽብር ቡድኑ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ከፈጸመው ሰብዓዊ መብት ጥሰት ባለፈ ሀብትና ንብረት ዘርፏል ብለዋል፡፡
ይህ ሁሉ ግፍ አልበቃው ብሎ በመከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ፈጽሞ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ያደረገው ሙከራ መንግስት በወሰደው ህግ የማስከበር ዘመቻ መክሸፉንና ቡድኑን በአጭር ጊዜ ውስጥ ዋሻ ውስጥ መግባቱን አስታውሰዋል፡፡
ወቅቱ ክረምት በመሆኑ የትግራይ አርሶ አደር እርሻውን ማከናወን እንዲችል መንግስት የተናጠል ተኩስ ቢያደርግም ህወሓት ወደሰላም ከመምጣት ይልቅ ህብረተሰቡን አስገድዶ በአማራና አፋር ክልሎች ወረራ አካሂዷል፡፡
የጥፋት ቡድኑ በክልሎቹ እየፈጸመ ያለውን ግፍና ጭቆና መንግስት ተገንዝቦ የተኩስ አቁሙን በማንሳት እርምጃ ለመውሰድ አቅጣጫ ማስቀመጡ ተገቢና የሚደገፉ መሆኑን አቶ አየለ ተናግረዋል።
መንግስት ያቀረበውን ጥሪ ተቀብለው እስከ ህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።
ሌላው የሆጤ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወጣት ብርሃኑ ይመር ፤ አሸባሪው ቡድን በህዝብ ላይ እየፈጸመ ያለውን ጥቃት ለመከላከል መንግስት አዲስ አቅጣጫ ማስቀመጡ እደግፋለው ብሏል።
በዚህም ከሠራዊቱ ጎን በመሰለፍ የሀገር ነጻነትና ሉዓላዊነት ለመጠበቅ መነሳሳቱን ነው የገለጸው፡፡
የመንግስትን ተኩስ አቁም ውሳኔ ተከትሉ አሸባሪው ከአማራና አፋር ክልሎች በርካታ ንጹሀን ዜጎችን መጨፍጨፉንና የተረፉትን ማፈናቀሉን አስታውሶ፤ ህወሓት ለቀጣይ ስጋት በማይሆን መልኩ ለመጨረሻ ጊዜ መደምሰስ ያስፈልጋል ብሏል፡፡
"አሸባሪው ቡድን ተጨማሪ ጥፋት እንዲፈጽም ዕድል መስጠት የለብንም'' ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ሽዋዬ ኃይሉ ናቸው፡፡
የመንግስትን ወቅታዊ ሀገራዊ ጥሪ ተቀብለው ወደ ግንባር በመዝመት ከሰራዊቱ ጎን ተሰልፈው በገባበት ገብተን ለመደምሰስ እንደተነሳሱ ነው ያስታወቁት።
ህዝብና ሀገርን ነጻ ማውጣት የሁላችንም ድርሻ ነው ብለዋል፡፡
በተለይ የጥፋት ቡድኑ በሴቶች ላይ የሚያደርሰውን ጥቃት ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቆም ወቅቱ አሁን መሆኑን ተናግረዋል።
ሀገር ለማዳን የተላለፈው የመንግስት ጥሪም የኢትዮጵያን ነጻነትና ሉዓላዊነት ለማጠበቅ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ነው ያመለከቱት።
መንግስት በአሁኑ ወቅት በአሸባሪው ላይ እርምጃ ለመውሰድ መገደዱንና የኢትዮጵያ ህዝብም የበረታ ክንዱን በጥፋት ቡድኑ ላይ እንዲያሳርፍ ጥሪ ማደረጉ ሚታወስ ነው፡፡