ቀጥታ፡

የአፋር ህዝብ የአሸባሪው ሃይል የጥቃት ሰለባ የሆነው ሀገሩን ከመፍረስ ለመታደግ በጀግንነትና በጽናት በመቆሙ ነው

ነሐሴ 06 ቀን 2013 (ኢዜአ) “የአፋር ህዝብ የአሸባሪው ሃይል የጥቃት ሰለባ የሆነው ሀገሩን ከመፍረስ ለመታደግ በጀግንነትና በጽናት በመቆሙ ነው” ሲል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገለጸ።

አስተዳደሩ ባወጣው መግለጫ ለአፋር ህዝብ ያለውን አጋርነት ገልጿል።

“ኢትዮጵያን ለማፍረስ ቆርጦ የተነሳው አሸባሪው የህወሃት ባንዳ ቡድን በእብሪት በከፈተብን ጦርነት ምክንያት ተፈናቅለው በአንድ አፋር ክልል በመጠለያ ጣቢያ በተጠለሉ 240 ሰላማዊ ዜጎች ላይ ልብ የሚሰብር ጥቃት ፈጽሟል” ብሏል።

የአስተዳደሩ አመራር እና መላ ነዋሪዎች አሸባሪው ሃይል በሰነዘረው የጭካኔ ጥቃት ህይወታቸውን ላጡ ኢትዮጵያውያን ጥልቅ ሃዘን እንደተሰማቸው ገልጾ፤ ለመላው ኢትዮጵያውያንና ለአፋር ህዝብና መንግስት መጽናናትን ተመኝቷል።

“የአፋር ህዝብ የአሸባሪው ሃይል የጥቃት ሰለባ የሆነው ሀገሩን ከመፍረስ ለመታደግ በጀግንነትና በጽናት በመቆሙ ነው” ያለው የአስተዳደሩ መግለጫ፤ “የህወሓት አሸባሪ ቡድን ሰሞኑን የአፋርን መስመር በመስበር ሀገራችንን ከጂቡቲ የሚያገናኘውን መንገድ ለመዝጋት ተደጋጋሚ ሙከራ አድርጓል” ብሏል።

ሙከራው የአፋር ልዩ ሃይሎችና ሚሊሻ ከመከላከያ ሰራዊት ጋር በመቀናጀት ባካሄዱት ውጤታማ የመከላከልና መልሶ ማጥቃት ትርጉም ባለው ደረጃ መክሸፉን ጠቅሷል።

“የአፋር፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት እና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎቻችን ባደረሱበት ኪሳራ ክፉኛ የተበሳጨው ሀገር አፍራሹ የህወሃት ባንዳ ከባድ መሳሪያ በመተኮስ የብቀላ እርምጃ የወሰደው ፊት ለፊት በሚፋለመው የሰራዊታችን ካምፕ ላይ ሳይሆን ከጦርነት ጥቃት ሸሽተው መጠለያ ጣቢያ ውስጥ በሚገኙ ተፈናቃዮች ላይ ነው” ሲል አስታውሷል።

አሸባሪው ሃይል የትግራይ ህጻናትን እያስገደደ በማስታጠቅ በጦርነት እሳት እንዲለበለቡ ማድረጉ ሳያንሰው ከጦርነት ሸሽተው መጠለያ ውስጥ በሚገኙ ንጹሃን ዜጎች ላይ ያደረሰው ጭፍጨፋ ኢ-ሰብዓዊነቱንና ህዝብ ጠልነቱን ዳግም ያረጋገጠበት እንደሆነ አመልክቷል።

አሸባሪው ህወሓት በአፋርም ሆነ በሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ የሚያደርሰው ጭፍጨፋ፣ በደልና ጉዳት የሚቆመው በመላው ህዝብ የጋራ ክንድ ሲደመሰስ ብቻ እንደሆነም ጠቁሟል።

“በኢትዮጵያ ሰማይ ስር አምባገነናዊ አገዛዝ በመትከል የጥቂቶችን ስግብግብ ፍላጎት እያሟላ ለመኖር የሚሻው የጥፋት ቡድኑ በእኛ መስዋዕትነት ካልተነቀለ ቀጣዩን ትውልድ ሲያስለቅስ የሚኖር ነቀርሳ ነው” ብሏል መግለጫው።

የአስተዳደሩ መግለጫ “የአፋር ህዝብና መንግስት ዛሬ የደረሰባችሁ የልብ ስብራት ሀገራችሁን ከመፍረስ ፤ልጆቻችሁን ዕድሜ ልክ ከማልቀስ የሚያድን ክቡር መስዋዕትነት መሆኑን ተገንዝባችሁ አሸባሪውን በመስበርና በመቅበር ዘመቻው ውስጥ እስካሁን ላሳያችሁት የጽናትና የጀግንነት መንፈስ ያለንን አድናቆትና አክብሮት እንገልጻለን” ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል።

አስተዳደሩና መላው ህዝብ ዘመቻው በድል እስኪጠናቀቅ በሁሉም መልክ ድጋፉ እንደማይለይም አረጋግጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም