ቀጥታ፡

መንግስት ሠራተኛው ሕዝብን በታማኝነት ካገለገለ ግንባር ላይ የሚፋለመውን የመከላከያ ሰራዊት የመደገፍ ያህል ነው

አዲስ አበባ፤ ነሃሴ 06/2013 (ኢዜአ) የመንግስት ሠራተኛው በየተሰማራበት የስራ መስክ የከተማውን ሕዝብ በታማኝነትና በቅንነት ካገለገለ ግንባር ላይ ያለውን የመከላከያ ሠራዊትንና ሌሎች ህግ አስከባሪዎችን የመደገፍ ያህል ነው ሲሉ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአገልገሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ ተናገሩ።

የአዲስ አበባ አስተዳደር ለሕልውና ዘመቻው ከ 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የአይነት ድጋፍ ማድረጉንም ገልጸዋል።

'ኢትዮጵያ አገሬ ናት' የሚል ሠራተኛ በሚያገለግልበት የስራ መስክ በንፅህናና በታማኝነት ሕዝቡን ማገልገሉ ጠላትን የመፋለሚያ አንደኛው መንገድ መሆኑን ነው የተናገሩት።

በዚህ ረገድ የመዲናዋን አገልግሎት አሰጣጥ በማዘመንና "እኔም ለሀገሬ ወታደር ነኝ" የሚለውን እሳቤ በአስተዳደሩ ሠራተኞች ዘንድ በማስረጽ የተገልጋዩን እርካታ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የከተማዋ ነዋሪ አገር ችግር ላይ በሆነችበት በዚህ ወቅት ለመከላከያ ሠራዊቱ አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ እያደረገ መሆኑንና በሕግ ማስከበር ዘመቻውም ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ የአይነትና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ አጋርነቱን ማሳየቱን አስታውሰዋል።

'ለዚህ ሕዝብ ከብልሹ አሰራር የፀዳና ተዓማኒነት ያለው አገልግሎት ይገባዋል' ያሉት አቶ ዣንጥራር ለከተማ አስተዳደሩ የስራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች የስራ መመሪያ ተሰጥቶ መግባባት ላይ ተደርሷል ነው ያሉት።

አሸባሪው ህወሓት ዳግም ትንኮሳ ከፈጸመ በኋላ እየተካሄደ ባለው የህልውና ዘመቻም እናቶች በየአካባቢያቸው ከስንቅ ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ከታቀደው ከ90 በመቶ በላይ ማሳካት እንደተቻለ አክለዋል።

የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ይታያል ደጀኔ በበኩላቸው ለመከላከያ ሠራዊቱ እየተደረገ ያለው ድጋፍና አጋርነት የኢትዮጵያዊያን ጠላትን በጋራ የመመከት እሴት ጎልቶ የታየበት ነው ብለዋል።

ድጋፉ አሸባሪውን ቡድን ለማጥፋት የቆራጥነት ወኔ ገንፍሎ የወጣበት፣ እናቶች ልጆቻቸውን ሳይሳሱ ለዘመቻ የሸኙበትና ወገባቸውን አስረው ስንቅ ያዘጋጁበት መሆኑን ገልጸዋል።

የመከላከያ ሠራዊቱን በቁሳቁስ፣ በሞራል፣ በገንዘብና በሰው ኃይል የማጠናከርና የመደገፍ ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉንና ከክፍለ ከተማው አገራዊ ጥሪውን የተቀበሉ  ወጣቶች መሸኘታቸውንም አክለዋል።

ነዋሪው ለሠራዊቱ ያለውን ቀና ኢ ድጋፍ በተግባር አሳይቷል ያሉት ደግሞ የጉለሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አባወይ ዮሃንስ ናቸው። 

በክፍለ ከተማው አገራዊ ጥሪውን የተቀበሉና ሠራዊቱን በመቀላቀል ለአገራቸው ለመመከት ፍቃደኛ የሆኑ በርከታ ወጣቶች ሽኝት ተደርጎላቸዋል ብለዋል።

አቶ አባወይ ነዋሪዎች የሚያደርጉትን ድጋፍ በተጠናከረ መልኩ ለመቀጠል ቁርጠኛ አቋም እንዳላቸውም ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም