የህልውና ዘመቻውን በተጠናከረ ክንድ እናስቀጥላለን - ኢዜአ አማርኛ
የህልውና ዘመቻውን በተጠናከረ ክንድ እናስቀጥላለን
ቡታጅራ ፤ ነሐሴ 6/2013 (ኢዜአ) ሀገር ለማፍረስ ግልጽ ጦርነት ያወጀውን አሸባሪው ህወሓት እስከወዲያኛው ለመደምሰስ የተጀመረውን የህልውና ዘመቻ በተጠናከረ ክንድ እናስቀጥላለን
የደቡብክልልየክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የተሳተፉበት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚመክር መድረክ ዛሬ በቡታጅራ ከተማ ተጀምሯል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳው በመድረኩ፤ የአሸባሪው ህወሓት ርዝራዥ በአፋር ክልል በንጹሃን ዜጎች ላይ የፈጸመውን አስነዋሪ ጭፍጨፋ የክልሉ ህዝብና መንግስት በእጅጉ አዝኗል ብለዋል።
ትናንት ይህችን ሀገር ሲመራ የነበረው ይሀው የጥፋት ቡድን ክህደት በመፈጸም የከፈተብንን ጦርነት ለመመከት ዳግም የተጀመረው የህልውና ዘመቻ ተገቢ መሆኑን ነው ያስታወቁት።
ህወሓት መከላከያን በመበተን ኢትዮጵያን አፈራርሳለው ብሎ በግልፅ ጦርነት ውስጥ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ መላው የሀገሪቱ ዜጋ በቁጣ መነሳቱን ጠቅሰዋል።
የክልሉ ህዝብና መንግስትም ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን የሀገሪቱን ህልውና ለማስጠበቅ አኩሪ ጀብዱ እየፈጸመ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
አሸባሪው ቡድን የኢትዮጵያ ጠላት የሆኑ አይዞህ ባዮቹን በመተማመን አሁንም ሀገር የማፍረስ ሴራውን አጠናክሮ በመቀጠሉ ይህንን ለመቀልበስ የክልሉ ህዝብና አመራሩ ከመቼውም ጊዜ በላቀ ዝግጁነት ወሳኝ ስራ አድርገው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የቡድኑን ሴራ ለማክሸፍ እየተካሄደ ያለውን የህልውና ዘመቻ ለማስቀጠል የክልሉ መንግሥት አበክሮ እየሰራ መሆኑንም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አረጋግጠዋል።
እስካሁን የክልሉ ህዝብ የህልውና ዘመቻውን ለማጠናከር 200 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብና በዓይነት ድጋፍ በማድረግ ደጀንነቱን ማሳየቱንና አሁንም ይህንን ተግባር አጠናክሮ ቀጥሏል።
የክልል ከፍተኛ አመራሮችም የአንድ ወር ደመወዛቸውን መለገሳቸውን ጠቅሰው፤ የመንግስት ሰራተኞችም የኑሮ ውድነቱ ሳይበግራቸው ለሰራዊቱ ያላቸውን አጋርነት መግለፃቸውን አስረድተዋል።
በሺህ የሚቆጠሩ የክልሉ ወጣቶችም በቁጭትና ወኔ ዘመቻውን ለመቀላቀል ያሳዩት ቁርጠኝነትና ጀግንነት የሚደነቅ መሆኑን ነው ርዕሰ መስተዳደሩ ያስታወቁት።
የክልሉ ልዩ ኃይልም በሁለት ዙር በመዝመት በግንባር ጀግንነቱን እያስመሰከረ ይገኛል።
የልማት ስራችን ለአፍታም ሳንዘናጋ ከመቼውም በላቀ ብርታት የወቅቱን የመኸር እርሻ እንቅሳቀሴንና የገቢ አሰባሰብ ሂደቱን ለማስፈጸም እየሰራን ነው ብለዋል።
በየደረጃው የሚገኘው የመንግስት መዋቅሩም በአገልጋይነት መንፈስ ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ ነው።
መድረኩም የተዘጋጀው ለህልውና ዘመቻው ስኬታማነት ህዝቡ እየተጫወተ ያለውን ሚና ማጎልበት በሚቻልበት ላይ እየተማከሩ ነው።