ኢትዮጵያ የገጠማትን የህልውና አደጋ ለመመከት ዝግጁ መሆኑን መኢአድ አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የገጠማትን የህልውና አደጋ ለመመከት ዝግጁ መሆኑን መኢአድ አስታወቀ
ነሐሴ 6/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የገጠማትን የህልውና አደጋ ለመመከት ዝግጁ መሆኑን የመላ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት / መኢአድ/ አስታወቀ።
መኢአድ አሸባሪው የህወሓት ቡድን እያደረሰ ያለውን አገር የማተራመስና የሽብር ተግባር አስመልክቶ ለኢዜአ መግለጫ ልኳል።
መግለጫውም አሸባሪው የህወሓት ቡድን እየፈጸመ ካለው አገር የማተራመስና የሽብር ተግባር ለመታደግ አባሎቹንና ደጋፊዎቹ ከመከላከያ ጎን በመሆን ለመመከት ዝግጁ መሆናቸውን አስውቋል።
የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ደም በመለገስ ለሰራዊቱ ያላቸውን አጋርነት አሳይተዋል፤ ድጋፋቸውንም አጠናክረው ይቀጥላሉ ብሏል የፓርቲው መግለጫ።
ፓርቲው አሸባሪው ህወሓት ለሰላሳ ዓመታት ሲያካሂደው የነበረውን የከፋፈለህ ግዛ ስርዓት በሰላማዊ መንገድ ሲታገል መቆየቱንም አመልክቷል።
መኢአድ የአገርን ህልውና ለማስቀጠል የፖለቲካ አጀንዳዎቹን በይደር ይዞ የአገር አድን ትግሉን በይፋ መቀላቀሉን አስታውቋል።
ሁሉም ኢትዮጵያ ባለው አቅምና በሚችለው ሁሉ አገር የማዳን ሃላፊነቱን እንዲወጣ ፓርቲው ጥሪውን አቅርቧል።
ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የተሰለፉ የውስጥም ይሁን የውጭ ታሪካዊ ጠላቶች ከእኩይ ተግባራቸው እንዲቆጠቡም ሲል መኢአድ አሳስቧል።
የሃገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ተከትሎ ኢኮኖሚ አሻጥር እየሰሩ የኑሮ ውድነቱን የሚያባብሱ ግለሰቦችን መንግስት እርምጃ መውሰድም ፓርቲው ጠይቋል።
አገርን ለማዳን የዘመቱና እየዘመቱም ላሉ ኢትዮጵያውያን ፓርቲው አጋርነቱን የገለጸ ሲሆን በጠላት አፍራሽ ፕሮፓጋንዳ ዜጎች መደናገር የለባቸውም ብሏል።
በአሸባሪው ህወሃት በአፋር ክልል በንፁሃን ላይ የተፈፀመውን ግዲያ መኢአድ ማዘኑን ገልፆ ድርጊቱን አውግዟል።
በተያያዘ ዜና እናት ፓርቲ በአፋር ክልል በፈንቲ ረሱ ዞን፣ በጋሊኮማ ከተማ፣ ጋሊኮማ ጤና ጣቢያ ጦርነት ሸሽተው በተጠለሉ ንጹሓን ላይ የህወሃት አሸባሪ ቡድን በፈፀመው ግዲያ ሀዘኑን ገልጿል።
እናት ፓርቲ በመግለጫው ከጦርነቱ ጋር ግንኙነት የሌላቸውና ሮጠው ማምለጥ የማይችሉ ሕጸናት፣ ሴቶችና አረጋውያን ላይ አሸባሪ ቡድኑ የፈፀመው ግዲያ "ቅስም ሰባሪ" ነው ብሏል።
እናት ፓርቲ፤ አሸባሪው ሕወሓት በታሪክ ይቅር የማይባል ወንጀል መፈጸሙን ይረዳል፤ በጽኑም ያወግዛል፤ በዓለም አቀፍ ሕግ በጦር ወንጀል ሊጠየቅ ይገባል ብሎም ያምናል" ብሏል በመግለጫው።
ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብና መገናኛ ብዙኃን ድርጊቱን በሚገባው ልክ እንዲያወግዙም እናት ፓርቲ ጠይቋል።
ፓርቲው ለተጎጂ ቤተሰቦች ለሚደረግ እገዛ ሁሉ አባላቱንና ደጋፊዎቹን በማስተባበር የአቅሙን አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል።
መኢአድ እና እናት ፓርቲ በንፁሃን ዜጎች ላይ በተፈፀመው ጭፍጨፋ የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ለተጎጂ ቤተሰቦች፣ ለክልሉ መንግስትና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ገልጸው መፅናናትን ተመኝተዋል።