የኢትዮጵያን ህልውና ለማስጠበቅ ዜጎች ሁሉ በጋራ መቆም አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ህልውና ለማስጠበቅ ዜጎች ሁሉ በጋራ መቆም አለባቸው
አዲስ አበባ፤ ነሀሴ 06 / 2013 (ኢዜአ) የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን የኢትዮጵያን ህልውና ለማስጠበቅ ዜጎች ሁሉ በጋራ እንዲቆሙ ጠየቀ።
የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኑ በዛሬው እለት ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮችን በማስመልከት መግለጫ ሰጥቷል።
የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኑ ሰብሳቢ ደራሲ ጌታቸው በለጠ፤ ኢትዮጵያን በገጠማት ወቅታዊ ችግር በፕብሊክ ዲፕሎማሲ ብዙ መሰራት ያለባቸው ጉዳዮች አሉ ብሏል።
በኢትዮጵያ ላይ የተጋረጠውን ወቅታዊ የህልውና ስጋት ለመመከት በአሁኑ ወቅት ሁሉም የጋራ አቋም በመያዝ ወደ አንድነት የመጣ በመሆኑ "መርገምቶች በረከትም" አለው ብሏል በመግለጫው።
በ2004 የሕዳሴ ግድብ ግንባታን ለመደገፍ የህዳሴ ምክር ቤት በሚል ከሁሉም ዘርፍ ታዋቂ ግለሰቦችን በማቀናጀት ተመስርቶ በሂደት ግን ወደ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ መለወጡን የቡድኑ አባል አርቲስት ደበሽ ተመስገን ገልጿል።
ቡድኑ ያለምንም የፖለቲካ ጣልቃገብነት የሚመራ ለአገር ጥቅም ማዕከል አድርጎ የሚሰራ ስለመሆኑም አብራርቷል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በሚመለከት ቡድኑ በርካታ የድፕሎማሲ ተግባራትን ማከናወኑን አስታውሷል።
የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኑ ግብፅን ጨምሮ በተለያዩ አገራት ተዘዋውሮ በድፕሎማሲው መስክ ውጤታማ ስራዎችን ሰርቷል ብሏል።
"ጥበብን ለሰላም" በሚል እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን ገልጹ፤ በአልጀዚራ የሚቀርብ ዘጋቢ ፊልምም በመሰራት ላይ መሆኑንም ጠቅሷል።
በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ የህዝብ ወገንተኛ በመሆን ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎችን ለመመከት ይበልጥ እንሰራለን ብሏል።
የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኑ አባል ወይዘሮ እንግዳዬ እሸቴ፤ ሱዳንን ጨምሮ አንዳንድ የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያዊያንን እርስ በርስ ለማጋጨት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
"በማጣላት እናስታርቅ" በማለት ከጀርባ የሚሰሩ በርካታ እኩይ ዓላማዎች መኖራቸውንም አንስተዋል።
የውስጥ ጉዳዮቻችን የሚፈቱበት የራሳችን የግጭት አፈታት የአሰራሮች እንዳሉ ጠቅሰው፤ በአገራችን ህጎችና ስርዓቶች መዳኘትና ችግራችን እንዲፈታ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኑ ይሰራል ብለዋል።
የአገር ሉዓላዊነት የተረካቢ ዜጎችን ሕይወት ለማዳበር እንሰራለን፣ ለሰራዊቱ ድጋፍ እናደርጋለን፣ የሕልውና ጉዳይ በመሆኑ ሁሉም ወገን አገርን ለማዳን ዘብ ሊቆም ይገባል ብለዋል።
ሌላኛው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኑ አባል ጋዜጠኞች ጥበቡ በለጠ፤ በኢትዮጵያ አንድነትና ሉአላዊነት ላይ አደጋ ተጋርጧል ለመመከት በጋራ መቆም አለብን ብሏል።