ኢትዮጵያን ካላፈረስኩ ብሎ የተነሳው አሸባሪው ህወሃት ለሃይማኖት ተቋማት ጭምር የሚራራ ማንነት የለውም

ጎንደር፤ነሐሴ 6/2013(ኢዜአ) ኢትዮጵያን ካላፈረስኩ ብሎ የተነሳው አሸባሪው ህወሃት ለሃይማኖት ተቋማት ጭምር የሚራራ በጎ ማንነት የለውም ሲሉ ነው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ህሩያን አባ ዮሴፍ ደስታ የገለጹት።

ቡድኑ ጥንታዊና ታሪካዊ በሆነው የዋልድባ ገዳም በፈጸመው ወረራ መነኮሳትን በአሰቃቂ ሁኔታ መግደሉን ማፈናቀሉንና ንብረት መዝረፉን ተናግረዋል።

የሽብር ቡድኑ ሐምሌ 28 ቀን 2013 ዓ.ም የገዳሙን ሁለት መነኮሳት በአሰቃቂ ሁኔታ በጥይት መግደሉን የገለጹት ስራ አስኪያጁ በሴት መነኮሳት ላይ ሳይቀር ድብደባና የአካል ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል።

በዚህም በገዳሙ ከሚኖሩ 1ሺህ 500 መደበኛ መነኮሳት መካከል ግማሾቹ ወደ ጎንደርና አጎራባች ወረዳዎች መሰደዳቸውን ጠቁመው፤ በገዳሙ ላይ በፈጸመው ወረራ የገዳሙን ንብረቶች ከመዝረፍ ባለፈ በቅርሶች ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑንም አስረድተዋል።

''ኢትዮጵያን ካላፈረስኩ ብሎ የተነሳ ሃይል ለሃይማኖት ተቋማት የሚራራ አይደለም'' ያሉት ስራ አስኪያጁ፣"ሁላችንም በሃይማኖት፣ በብሔር፣ በፖለቲካና በማህበረሰብ ልዩነት ሳንታጠር የሽብር ቡድኑን ሴራና ተንኮል ማክሸፍ አለብን” ብለዋል፡፡

ገዳሙ ለረዥም ጊዜ ጠብቆና ተንከባክቦ ያቆየውን የተፈጥሮ ደን ማውደሙን የገለጹት ሃላፊው፣ የገዳሙ መነኮሳት ንብረት የሆኑ የእርሻ፣ የከብት እርባታና የአትክልትና ፍራፍሬ ልማቶችን ማውደሙንም ገልጸዋል፡፡

"የሽብር ቡድኑ ኢትዮጵያን ለማፈራራስ፣ ህዝቡንም ለመበታተን እንዲሁም የሃይማኖት ተቋማትን ለማዳከም የተነሳበት ጊዜ በመሆኑ ኢትዮጵያዊያን ዛሬም ሕብረታችንን በማጠናከር ሀገር እናድን" ሲሉም አባ ዮሴፍ ጥሪ አቅርበዋል።

ቡድኑ በስልጣን ዘመኑ በሃይማኖት ተቋማት ጣልቃ በመግባት የተለያየ ስም በመስጠት ምዕመናኑን ሲከፋፍል ሲያጋጭ መቆየቱን ጠቅሰው ይሔንንም የህልውናው ማቆያ አድርጎ ሲሰራበት እንደነበረ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ካድሬዎቹንና የደህንነት አባላቱን መነኩሴ፣ ዲያቆን፣ ካህን፣ የአብነት ተማሪ፣ ሼህ ኡለማና ደረሳ አስመስሎ በሃይማኖት ተቋማት አስርጎ በማስገባት አማኞችና የሃይማኖት አባቶችን በመከፋፈል ሲያጣላ እንደነበረም አስታውሰዋል።

ከስልጣን ከተባረረ ማግስት ጀምሮ የሃይማኖት ተቋማትን የጦር ምሽግና መዋጊያ በማድረግ ተቋማቱ በጉዳት እንዲፈርሱና ቅርሶቻቸው እንዲወድሙ በማድረግ ታሪክ ይቅር የማይለው ነውረኛ ድርጊት እየፈጸመ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

"በመሆኑም ማንኛውም እምነት የምንከተል ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ድርጊቱን አጥብቀን ልናወግዝ ይገባል"ሲሉም ጥሪ አስተላልፈዋል። 

"ወቅቱ የፖለቲካና የማንነት ጉዳይ ሳይሆን ኢትዮጵያዊነትና የህልውና ጉዳይ ብሎም የመኖርና ያለመኖር በመሆኑ ሁላችንም በአንድነት በመቆም በሀገራችን የበቀለውን ይህን ክፉ አረም ማስወገድ ይገባል" ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡ 

በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የዋልድባ ገዳም በ485 ዓ.ም መቋቋሙን ከሀገረ ስብከቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም