ቀጥታ፡

ለተጀመረው የህልውና ዘመቻ ስኬት አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን

ጋምቤላ፣ ነሐሴ 05 ቀን 2013 (ኢዜአ) የአሸባሪው የህወሓት ቡድን ሀገር ለማፍረስ የከፈተብንን ጦርነት ለመቀልበስ ለተጀመረው የህልውና ዘመቻ ስኬት አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል ዝገጁ ነን ሲሉ የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች አስታወቁ።

አሸባሪ ቡድኑ ቁሜለታለሁ ለሚለው የትግራይ ህዝብ የሚያስብ ቢሆን ህፃናትን በጦርነት ከመማገድ ተቆጥቦ የተናጥል የተኩስ አቁም ውሳኔን እንደ እድል ይጠቀም ነበር ነው ሲሉ ነዋሪዎቹ አውስተዋል።

ነዋሪዎቹ አሸባሪው የህወሓትን ርዝራዥ ከትግራይ ህዝብ በመነጠል ለማስወገድ የሚደረገውን ትግል በመደገፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል።

"አሸባሪ ቡድኑ ለትግራይ ህዝብ የሚያስብ ቢሆን ህፃናትን ለጦርነት ከመማገድ ተቆጥቦ ለህዝቡ ሰላምና ደህነነት በሰራ ነበር" ብለዋል።

አሸባሪ ቡድኑ በአፋርና በአማራ ክልሎች ወረራ በመፈጸም በንጹሀን ላይ የፈጸመውን ጥቃት አውግዘዋል።

መንግስት ትዕግስቱ አሸባሪውን ለማስወገድ ትናንት ያስተላለፈውን ሀገራዊ ጥሪ በመደገፍ ለስኬታማነቱ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ መነሳሳታቸውን አስታውቀዋል።

"አሸባሪው የህወሓት ቡድን የለመደው ዘረፋ ቀርቶበት እንጂ ለህዝብና ለሀገር የሚያስብ ቢሆን ኑሮ በመሰረተ ልማት አውታሮችና ዜጎች ላይ አሰቃቂ ጉዳት አያደርስም ነበር" ነው ያሉት።

የሽብር ቡድኑ ጦርነት የከፈተው ለትግራይ ህዝብ  አስቦ ሳይሆን በህዝብ ግፊት ያጣውን ስልጣን  ለማስመለስ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም ዋነኛ ማሳያው በትግራይ ክልል በጊዜዊ አስተዳደር የተወከሉ የትግራይ ተወላጆችን በግፍ መግደሉና የነገ ሀገር ተረካቢ ህፃናትን ለጦርነት መማገዱን ጠቅሰዋል።

አሸባሪ ቡድኑ ባለፉት 27 ዓመታት ጋምቤላን ጨምሮ በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች እንደፈጸው ግፍና በደል ሂሳብ ማወራረድ ካለበት ኢትዮጵያ ህዝብ ሆኖ እያለ ሒሳብ እናወራዳለን የሚለው የሚሳዝን ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም