አንድነታችንን በማጠናከረ ሽብርተኛውን ቡድን እንደመስሰዋለን! - ኢዜአ አማርኛ
አንድነታችንን በማጠናከረ ሽብርተኛውን ቡድን እንደመስሰዋለን!
ሐረር ነሐሴ 5/2013 (ኢዜአ) አንድነታችንን አጠናክረን ከመከላከያ ሠራዊታችን ጎን በመሰለፍ ሽብርተኛውን የትህነግ ቡድን እንደመስሰዋለን ሲሉ የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ነዋሪዎች አሰታወቁ።
ከዞኑ 24ቱ ወረዳዎችና ከተሞች የተውጣጡ ነዋሪዎች ይህንን ያሉት ሰራዊቱ የሚደግፍና አሸባሪውን የሚያወግዝ ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ በሐረማያ ከተማ ባካሄዱበት ወቅት ነው።
ሰልፈኞቹ የመከላከያ ሠራዊታችን ጎን ተሰልፈን ሽብርተኛውን የትህነግ ቡድን እንደመስሰዋለን፣ ቡድኑ በዜጎች ላይ እየፈፀመ ያለውን ግፍ በፅኑ እንቃወማለን፣ ክብርና ሞገስ ውድ ህይወታቸውን ለሰጡ መከላከያ ሰራዊት አባላት የሚሉ መልዕክቶችን አሰተላልፈዋል።
እኛ ኢትዮጵያውያን ሰላማችንን በማስጠበቅ ልማታችንን እናረጋግጣለን፣ የህልውናችን መሠረት የሆነው የህዳሴ ግድባችን ግንባታን እስከመጨረሻው በመደገፍ ከዳር እናደርሳለንም ብለዋል።
የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሁሴን ፈይሶ በወቅቱ “ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚንቀሳቀሰውን ሽብርተኛውን የህውሃት ቡድንን አንድነታችንን በማጠናከር እንደመስሰዋለን” ብለዋል።
የውስጥ ተላላኪዎቹን ነቅለን ካወጣን ጦርነቱን በአጭር ጊዜ በድል እናጠናቅቃለን፤ታላቅ ኢትዮጵያንም እንገነባለን ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮዽያን ማጠናከር ማለት ከጀግናውን መከላከያ ሰራዊት ጎን መሰለፍ ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፣ ሕዝቡ ለሠራዊቱ የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያጠናክርም መልዕክት አስተላልፈዋል
ሽብርተኛውና ተላላኪዎቹ የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት እንደተጠናቀቀና በአዲሱ ዓመትም ''ተላላኪ ያልሆነ፣ጠንካራና እጅ የማይሰጥ መንግሥት'' እንደሚቋቋም ተናግረዋል።
ሰልፈኞቹ በሰጡት አስተያየት ሀገር ለማፍረስ የሚጥረውን ሽብርተኛው ቡድንና ተላላኪዎቹን ለመዋጋት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
መንግሥት የጀመረውን የማጥቃት እርምጃም በመደገፍ እንደሚዘምቱ አረጋግጠዋል።
በሰልፉ ወጣቶች፣ሴቶች፣አርሶ አደሮች፣የሀገር ሽማግሌዎችና የሐይማኖት አባቶች ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የአገር አንድነትና ሉዓላዊነትን ለማስከበር በሚደረገው እንቅስቃሴ ሁለንተናዊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑ ይታወቃል።