ኢትዮጵያን ከወራሪ ጠላት ለመታደግ እንዘምታለን - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን ከወራሪ ጠላት ለመታደግ እንዘምታለን
ሀዋሳ፤ ነሐሴ 05/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን ከወራሪ ጠላት ለመታደግ በሚደረገው የህልውና ዘመቻ ለመሳተፍ እንዘምታለን ሲሉ የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር ሠራተኞች አስታወቁ ።
መንግስት ትናንት ያስተላለፈውን ሀገራዊ ጥሪ ተከትሎ የኢዜአ ሪፖርተር ካነጋገራቸው ሠራተኞች መካከል የአስተዳደሩ ዐቃቤ ሕግ መምሪያ ባልደረባ ወይዘሮ ሕይወት ቤላሞ ፤ አሸባሪው ህወሓት በስልጣን ዘመኑ ኢኮኖሚያዊ አሻጥር በመፈፀም ኢትዮጵን በመበዝበዝ ህዝቦቿን እርስ በእርስ ሲያባላ ኖሯል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያን የማፈራረስ አጀንዳውን ለማራመድ የትግራይን ህዝብ ከእህት ወንድሙ በመነጠል የከፈተው ጦርነት ህዝባዊ ገጽታ ለማላበስ እየጣረ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁን ወቅት ቡድኑ እየተፈጸመ ያለውን ወረራ ለማስቆምና ቡድኑን ዳግም ለመደምሰስ የፌደራል መንግስት ያስቀመጠው አቅጣጫ ተገቢነት አለው ብለዋል።
"ሁሉንም ነገር ማከናወን የምንችለው ሀገር ስትኖር ነው" ያሉት ወይዘሮ ሕይወት፣ ሀገርን ለማዳን በሚያስፈልገው ሁሉ ለመሳተፍ ወደ ኋላ እንደማይሉ አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያን ለማዳን መቼም፣ የትም፣ በማንኛውም ሁኔታ እስከ ግንባር ድረስ ለመዝመት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ወይዘሮ ሕይወት ፤ እስካሁንም በሚሰሩበት መስሪያ ቤት በኩል የወር ደመወዛቸውን ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ አድርገዋል።
በአስተዳደር የገቢዎች ባለሥልጣን ቅርንጨፍ ጽህፈት ቤት ባለሙያ ወይዘሮ ሕይወት ከበደ፤ ህወሓት ለተቀሩት የኢትዮጵያ ህዝቦች ብቻ ሳይሆን ቆሜለታለሁ ለሚለው ለትግራይ ህዝብም ጠላት ነው ብለዋል።
መንግስት የትግራይ አርሶ አደር ወደ እርሻ ሥራውና መደበኛ እንቅስቃሴው እንዲመለስ በማሰብ የሰጠውን የጥሞና ጊዜ ህወሓት አሰናክሏል።
"የተለመደውን የሽብር ተግባሩን አጠናክሮ በመቀጠል ለህዝብ ያለውን ንቀት በተደጋጋሚ በተግባር አሳይቷል" ብለዋል።
ይህንን ኃይል ለማጥፋትና ኢትዮጵያን ለማዳን በገንዘብና በዓይነት ከሚያደርጉት ድጋፍ ባለፈ በዘመቻው በመሳተፍ ለመንግስት ወቅታዊ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ተነሳስተዋል።
"አሸባሪው ህወሓት እኔ ያልመራኋት ኢትዮጵያ ትፍረስ" በሚል አቋም ይዞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ባለሙያ አቶ ሰሙንጉስ ቦልካ ናቸው።
"ቡድኑ ይህን ዓላማውን ለማስፈጸም ከውጪ ጠላቶች ጋር ጥምረት ፈጥሮ እየሰራ በመሆኑ በአፋጣኝ ሊወገድ ይገባል" ብለዋል።
ይህን ባንዳ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ መንግስት ያቀረበው ጥሪ በመደገፍ እዘምታለሁ ሲሉም አስታውቀዋል።
"አሁን ላይ በየግንባሩ በጀግንነት እየተዋደቁ ያሉ የቁርጥ ቀን ልጆች እየሰሩ ያሉት ሀገር ለማዳን በመሆኑ ሁላችንም ተባብረን ከሠራዊታችን ጎን ልንቆም ይገባል" ብለዋል አቶ ሳሙኤል።