ዩኒቨርሲቲው ለምርምርና ቴክኖሎጂ የስርፀት ተግባራት የሚያገለግል ህንፃ ሊያስገነባ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው ለምርምርና ቴክኖሎጂ የስርፀት ተግባራት የሚያገለግል ህንፃ ሊያስገነባ ነው
አዲስ አበባ ግንቦት 8/2010 የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ለምርምርና ቴክኖሎጂ ስርፀት ተግባራት የሚያገለግል ህንፃ ለመገንባት እየተዘጋጀ መሆኑን ገለጸ። ዩኒቨርሲቲው አሁን ባለው ህንፃ የኒውክሌር ግንባታ፤ የባዮ ቴክኖሎጂዎች፤ ዘላቂ የኃይል አቅርቦትና ሌሎች የልህቀት ማዕከላትን አቋቁሞ እየሰራ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ኑርልኝ ተፈራ በተለይ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ገልፀዋል። ግንባታው በመጪው ዓመት መስከረም ወር ተጀምሮ በ18 ወራት ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው አዲሱ ህንፃ፤ እነዚህን ጨምሮ ዩኒቨርሰቲው ላቋቋማቸው ሌሎች ስምንት የልህቀት ማዕከላትና ሶስት ግዙፍ የቤተ-ሙከራ ተግባራት ማከናወኛ የሚውል ነው ብለዋል። ለማዕከላቱ የሚሆኑ መሳሪያዎች ከውጭ ተገዝተው ወደአገር እየገቡ መሆናቸውን ያመለከቱት ፕሬዝዳንቱ፤ የሰው ኃይል ተደራጅቶ የምርምር ንድፈ-ሀሳቦች ከወዲሁ መቅረብ መጀመራቸውን ተናግረዋል። የልህቀት ማዕከላቱ የሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች የምርምር ስራዎቻቸውን የሚያከናውኑባቸው፤ ሌሎች ምሁራን የሚመራመሩባቸው እንዲሆኑ ይደረጋል ያሉት ዶክተር ኑርልኝ የቤተ-ሙከራ ማዕከላቱ ደግሞ የኬሚካል፣ የስነ-ህይወትና የግንባታ ቁሶች ምርመራ የሚከወንባቸው መሆናቸውን ገልፀዋል። "ቤተ-ሙከራዎቹ ግዙፍና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ በመሆናቸው ሁሉም ቦታ አይገኙም፤ በመሆኑም ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በተጨማሪ ማንኛውም ተመራማሪ ሊጠቀምባቸው ይችላል" በማለት ዶክተር ኑርልኝ አስታውቀዋል።