ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና የህዝቦቿን ደህንነት ለማስጠበቅ የድርሻችንን እንወጣለን

ነሐሴ 05 ቀን 2013 (ኢዜአ) "የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም፣ የህዝቦቿን ደህንነት ለማስጠበቅ ሁላችንም የድርሻችንን እንወጣለን" ሲሉ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሠራተኞች ገለጹ።

ሠራተኞቹ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የሚደረገውን ድጋፍ አጠናክረው ለመቀጠል ቃል ገብተዋል።

የተቋሙ አመራር አባላትና ሠራተኞች ለአገር መከላከያ ሠራዊት የደም ልገስና የአንድ ወር የደመወዝ ድጋፍ አድርገዋል።

"በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ለማፍረስ በውጭና በውስጥ ጠላቶች እየተካሔደ ያለውን ሴራ ለማክሸፍ በጋራ መረባረብ ይጠበቅብናል" ብለዋል። 

ኢትዮጵያዊያን ከመቼውም ጊዜ በተለየ ለሰራዊቱ ደጀን ከመሆን ባሻገር በየተሰማራንበት የሙያ ዘርፍ ጠንክሮ በመስራት አገርን መታደግ ይጠበቅብናል" ሲሉም ገልጸዋል።

በመሆኑም የሀገሪቱን ሕልውና ለማስጠበቅ ቅድሚያ ሰጥተው ዓቅማቸው በፈቀደው መጠን አገርን ከችግር ለማውጣት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አሸብር በላቸው በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ወቅቱ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን በመቆም ድጋፍና አለኝታነትን በተግባር ማረጋገጥ የሚያስፈልግበት ነው።

ኢትዮጵያ በውስጥና በውጭ የተደቀነባትን ችግርና ፈተና ለመሻገር የሁሉም ዜጋ ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ ተቋማቸው ይሕንኑ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለመከላካያ ሰራዊት ያልተቋረጠ ድጋፍ ለማድረግ የተቋሙ ሰራተኛና አመራር እንቅስቃሴ እያደረጉ እንደሆነም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም