ቀጥታ፡

በውጭ ሃይሎች በኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ያለው ጫና ዜጎችን አንድ አድርጓል-- ፀሐፈ ተውኔትና ገጣሚ አያልነህ ሙላቱ

ነሀሴ 5/2013 (ኢዜአ) የህወሓትን አሸባሪ ቡድን በሚደግፉ የውጭ ሃይሎች በኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ያለው ጫና ዜጎችን አንድ አድርጓል ሲል አንጋፋው ፀሐፈ ተውኔትና ገጣሚ አያልነህ ሙላቱ ገለጸ።

የኢትዮጵያ ህዝብ በየትኛውም ጊዜ በሚያጋጥም የጠላት ተንኮሳ በጋራ በመቆም በመመከት አንድነቱን በተደጋጋሚ አሳይቷል ብሏል።

'ኢትዮጵያ በታሪኳ ማንንም አገር በሃይል ወራም ሆነ  ጭቆና ለማድረስ ሞከራ አታውቅም' የሚለው ባለቅኔው አያልነህ ሙላቱ፣ ጠላቶቿ ግን በየዘመኑ ወረራና ጥቃት ሲፈጽሙባት እንደኖሩ ጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ስንቅ ሰንቆ፣ በጎበዝ አለቃ ተደራጅቶ ጠላቶቹን እየመከተ የአገሩን ሉዓላዊነት አስከብሮ ያቆየ ጀግና ህዝብ መሆኑን ተናግሯል።

ኢትዮጵያ ውስጣዊ ችግር ላይ ሆና እንኳን ''በሶማሊያው ወረራ ወቅት ከ300 ሺህ በላይ ገበሬ ሞፈሩን ሰቅሎ የጠላትን ጦር ብትንትኑን አውጥቷል' ብሏል ባለቅኔው አያልነህ ሙላቱ።

የኢትዮጵያ ውስጣዊ ችግሮች ተገን በማድረግ የተለያዩ የውጭ ሃይሎች አሁን ላይ ጫና እያደረጉ መሆኑን ሁሉም ይገነዘባል ብሏል።

ኢትዮጵያን ለመበታተን ብሎም የጀግንነትና የፀረ-ቅኝ ግዛት ድል ታሪኳን ለማጥፋት እየሰሩ መሆኑን ጠቅሷል።

በመሆኑም የውጭ ጠላቶችን ጫና በተቀናጀ መልኩ በመመከት ሂደት ሁሉም በጋራ ሊቆም ይገባል ነው ያለው።

የውጭው ጫና አንድም በአባይ ወንዝ እንዳትጠቀም በሌላ በኩል ለራሳቸው ጥቅም ኢትዮጵያን ለመጉዳት የሚያካሂዱት ሴራዎች መሆናቸውን አብራርቷል።

የውጭ ሃይሎችን ጫና ለመመከት የኪነ- ጥበብ ባለሙያዎችም በአገር በቀል እውቀት ችግሮችን በመፍታት ረገድ ማህበረሰቡን የማስተማር ስራ ማከናወን ይገባቸዋል ብሏል።

ኢትዮጵያውያንን አንድ የሚያደርጋቸው ጦርነት ብቻ ሳይሆን የባህል፣ የኪነ ጥበብ፣ እሴትና የማንነት መወራረስ እንደሆነም አብራርቷል።

ኢትዮጵያዊያን ውስጣዊ ችግሮች ሲከሰቱ የሚፈቱበት የቆየና የካበተ ልምድ እንዳላቸው ጠቅሶ አሁን ያጋጠመው ችግርም ይፈታል ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም