ቀጥታ፡

የኢዜአ ሰራተኞች ለአገር መከላከያ ሰራዊት የአንድ ወር ደሞዛቸውንና ደም ለመለገስ ቃል ገቡ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 5/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት /ኢዜአ/አመራሮችና ሰራተኞች ለአገር መከላከያ ሰራዊት የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለመስጠትና ደም ለመለገስ ቃል ገቡ።

የኢዜአ ሰራተኞች በሙያቸውም ከሰራዊቱ ጎን በመሆንና ግንባር ድረስ በመሄድ የሰራዊቱን ጀግንነትና እየፈጸመ ያለውን ተጋድሎ ለህዝብ ለማድረስ እየሰሩ ይገኛሉ።

ሰራተኞቹ በአገራዊ ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ምክክር ያደረጉ ሲሆን፤ የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለሰራዊቱ ለመስጠት ቃል ገብተዋል።

ከገንዘብ ልገሳው በተጨማሪ ሙያዊ ሃላፊነታቸውን ለመወጣት ተጨማሪ ጊዜ ሰጥተው እንደሚሰሩ ገልጸው፤ እስከ ግንባር በመዝመት ሰራዊቱን ለመቀላቀል ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያን ለማዳን ሲል እየተዋደቀ ለሚገኘው የአገር መከላከያ ሰራዊት ደማቸውን እንደሚለግሱም ገልጸዋል።

"ኢትዮጵያን ለማዳን ጊዜው አሁን ነው፤ አገራችንን ከአፍራሹ አሸባሪ ቡድን ለመጠበቅ ከሰራዊቱ ጎን ለመቆም ዝግጁ ነን፤ እያንዳንዳችን የአንድ ወር ደሞዛችንን ለመስጠት ዝግጁ ነን" ሲሉም አረጋግጠዋል።

አሸባሪው ሀገርን ለማፍረስ በተለያዩ መልኩ እየሰራ ነው ያሉት ሰራተኞቹ፤ በማህበራዊ ሚዲያ ሀገር ላይ የተከፈተውን ዘመቻ ከመመከት አንጻርም የሚጠበቅባቸውን ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሰራተኞቹ ከዚህ ቀደም ሲሰራበት በነበረው የስራ ሞራል እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተፈራ በቀለ በሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያ በሁሉም መልክ አሸናፊ እንድትሆን አንድነታችንን መጠበቅ ይኖርብናል ብለዋል።

ሀገርን ለማፍረስ እየሰራ ያለውን አሸባሪ በሁሉም ረገድ ድጋፍን በማጠናከር መመከት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ላይ ተከፈተውን ዘርፈ ብዙ ዘመቻ ማሸነፍ የሚቻለው በተባባረ ክንድ በጋር ስንሰራ ነው በማለት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ቤተልሄም አበባው ገልጸዋል።

በዚህም ሁሉም የተቋሙ ሰራተኛ በማህበራዊ ገጹ ስለ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን እውነተኛ መረጃ ለዓለም ማድረስ እንዳለበትም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ የተቋሙ ሰራተኞችና አመራሮች ለመከላከያው ደጀን ለመሆን ያሳዩትን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።

ከዚህ ቀደም በህግ ማስከበር ዘመቻው ሰራተኞቹ አገርን ከማዳን አንጻር እስከ ግንባር በመሄድ የተለያዩ ዘገባዎችን ሲሰሩ መቆየታቸውን አንስተዋል።

"ኢትዮጵያ የምትሻገርበት ወሣኝ ጊዜ አሁን ነው" ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤የህወሃትን አሸባሪ ቡድን በማስወገድ የኢትዮጵያን ብልጽግና ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

ከዚህ አኳያ የኢዜአ ሰራተኞችና አመራሮች ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢዜአ ሰራተኞችና አመራሮች ከዚህ ቀደም ለህዳሴው ግድብና ለገበታ ለሀገር ድጋፍ ማድረጋቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም