ቀጥታ፡

የአሶሳ ነዋሪዎች ህወሃት ለመጨረሻ ጊዜ እንዲደመሰስ የተላለፈውን ውሳኔ እንደሚደግፉ አስታወቁ

አሶሳ ፤ ነሐሴ 05 / 2013 (ኢዜአ) አሻባሪው ህወሃት ለመጨረሻ ጊዜ እንዲደመሰስ የፌደራል መንግስት ያስተላለፈውን ውሳኔ እንደሚደግፉ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች አስታወቁ፡፡

አስተያታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የከተማው ነዋሪዎች መካከል አቶ ኢብራሂም አዙቤር፤  አሁን ኢትዮጵያን እየመራ የሚገኘው መንግስት ህዝባዊ መሠራት አለው ነው ያሉት፡፡

መንግስት የህዝብን ፍላጎት መሠረት በማድረግ ሀገር እየመራ ነው ያሉት አስተያየት ሰጪ፤  ይህም ለህዝብ ጥቅም እና ደህንነት ቅድሚያ መስጠቱን እንደሚያመለክት ተናግረዋል፡፡

አሸባሪው ህወሃት ግን ህዝብ የታገለለትን ዓላማ ለግል ጥቅሙ  በማዋል  ለአገር ሠላም የተሰውትን ዜጎች ረስቷል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ ህወሃት ምን ያህል መጥፎ እንደሆነ በሚገባ ተረድቷል ያሉት አቶ ኢምራሂም ፤ፋሽስት ኢጣሊያን ለመደምሰስ እንደተነሳው ሁሉ በአሸባሪው ቡድኑ ላይ ቆርጦ ተነስቷል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ህወሃት ግን ይህንን ሃቅ አሁንም አልተረዳውም፡፡

የመንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም ስምምነት በግሌ እደግፋለሁ፤  ከዚህ ውሳኔ የደረስኩት ለሰው ልጅ ከምንም በላይ ሠላም ስለሚያስፈልገው ነው ብለዋል፡፡

የሽብር ቡድን እስኪወገድ የትኛውንም ድጋፍ አደርጋለሁ ብለዋል፡፡

የህወሃትን ሃገር የማፍረስ ሴራ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ በተጠራው ክተት ሁሉም የትግራይ ተወላጆች ሊሳተፉ ይገባል ሲሉም  መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ እንቅስቃሴ በተቃራኒ የሚቆሙ ካሉም የሽብር ቡድኑ ደጋፊ ሊሆኑ እንደሚችሉ አቶ ኢብራሂም ጠቅሰዋል፡፡

መንግስትም በውስጡ ሆነው ህወሃትን የሚደግፉ ጥቂት ግለሰቦች ሊኖሩ ስለሚችሉ ማጥራት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

አቶ ዘውዱ አበባው በበኩላቸው ፤የመንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔም  ሆነ የተኩስ አቁሙ ማብቃት አግባብ እና እንደሚደግፉ ተናግረዋል፡፡

ሆኖም  በተናጠል የተኩስ አቁሙ የትግራይ ህዝብ እንዲጠቀም የተቀመጡ ዓላማዎች ግባቸውን እንዳልመቱ ጠቁመው ምክንያቱ ደግሞ የአሸባሪው ርዝራዥ ነው ያሉት፡፡

ህወሃት ለትግራይ ህዝብ ጭምር እንደማይበጅ በግልጽ አሳይቷል ያሉት አቶ ዘውዱ፤ ቡድኑን ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ ለተጀመረው እንቅስቃሴ ሁሉም ዜጋ  ከመከላከያ ሠራዊት ጎን መቆም እንዳለበት አመልክተዋል፡፡

ህወሃት ሃገርን እንደ ትንሽ መንደር በመቁጠር አፈርሳለሁ ብሎ መነሳቱ አስገራሚ እና መቼም የማይቻል ነው ያሉት ደግሞ አቶ አበበ ፈቃዱ የተባሉ ነዋሪ ናቸው፡፡

የፌደራል መንግስት የተሰጠውን የጥሞና ጊዜ የትግራይ ህዝብ እንዳይጠቀም አሸባሪው ማደናቀፉን ጠቁመው፤ እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን እያለ ለዘመናት በሃይል ገዝቷል ብለዋል፡፡

ይህ አካሄዱ የዜጎችን ህይወት ቀጥፏል፤  አሁንም ለውጊያ ያልደረሱ ህጻናትን ጭምር  ለጦርነት እየማገደ ህብረተሰቡን  ቀውስ ውስጥ መክተቱን ተናግረዋል፡፡

በትግራይ አጎራባች በሆኑ አማራ እና አፋር ክልሎች ባደረገው ትንኮሳ ያጠፋው የሰው ህይወት እና ያወደመው ንብረትም ነዋሪው ጠቅሰዋል፡፡

ሌላው ነዋሪ ቄስ ደስዬ ወዳጄ፤  ማንም ኢትዮጵያዊ ጦርነት እንደማይፈልግ አመልክተው፤

ጥቂት የህወሃት የጥፋት ቡድን አባላት የፖለቲካ ጥቅማቸውን ለማሳካት ህብረተሰቡን አስገድደው ወደ ጦርነት እየማገዱ ነው ብለዋል፡፡

የትግራይ ወጣቶችን ጨምሮ ህዝቡን አስገድዶ ወደ ጦርነት በማስገባት የሃይማኖት ተቋምት እና ንብረት ለማውደም መነሳሳቱ አሳዛኝ እና የሚወገዝ ተግባር መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም