አሸባሪውን ህወሃት ለመደምሰስ ለተጀመረው ሀገራዊ ዘመቻ ስኬታማነት ድጋፋችን ይቀጥላል - የድሬዳዋ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪውን ህወሃት ለመደምሰስ ለተጀመረው ሀገራዊ ዘመቻ ስኬታማነት ድጋፋችን ይቀጥላል - የድሬዳዋ ነዋሪዎች
ድሬዳዋ፣ ነሐሴ 05 ቀን 2013 (ኢዜአ) "አሸባሪውን ህወሃት ለመደምሰስ ለተጀመረው ሀገራዊ ዘመቻ ስኬታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጋችንን እንቀጥላለን" ሲሉ የድሬዳዋ ነዋሪዎች አስታወቁ።
እናቶች ለሠራዊቱ ስንቅ ከማዘጋጀት ባሻገር ለአገር ሰላምና ለኢትዮጵያ ጠላቶች መወገድ እየፀለዩ ነው።
ሀገራዊ ጥሪውን ተከትሎ ኢዜአ ያነጋገራቸው የድሬዳዋ ነዋሪዎች፤ ጦረኝነትን መፍትሄ ያደረገውን የሽብር ቡድኑን ማስወገድ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።
የአካባቢያቸው ሰላም በአሸባሪው ተላላኪዎች እንዳይታወክ እየተቆጣጠሩ እንደሚገኙም አመልክተዋል።
የእግር ኳስ አሰልጣኟ መሠረት ማኔ "ሠራዊቱ ሀገርን ለማፍረስ የሚጣጣረውን የአሸባሪው ርዝራዥ ለመደምሰስ የጀመረውን ተልዕኮ ለማሳካት አስፈላጊውን ድጋፍ አደርጋለሁ" ብላለች።
ለሀገር ሰላም፣ ለህዝብ ደህንትና ልማት መረጋገጥ መንግስት የሰጠውን ዕድል በመናቅ ህወሃት ህጻናትን ለጦርነት መማገዱ የሚወገዝ ተግባር እንደሆነም አመልክታለች።
"ይህም ቡድኑ ሀገር የማፍረስ ተልዕኮ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይና አለም አቀፍ መንግስታት ጭምር ሊያወግዙት የሚገባ ወንጀል ነው" ስትል ገልጻለች።
"ቡድኑን ለመደምሰስ በጉልበት፣ በዕውቀትና በገንዘብ አስተዋጽኦ በማድረግ ከሠራዊቱ ጎን እንቆማለን" ብላለች።
የቀድሞ የአየር ኃይል ሠራዊት አባል ግርማ ትቶኝ፤ የመከላከያ ሠራዊት ላይ ህወሃት የፈፀመው ጥቃት ከሃዲነቱን የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
"ይህንን ባንዳ ለመደምሰስ የቀድሞ ሠራዊት፣ የአየር ኃይል አባላት አስፈላጊውን መስዋትነት ለመክፍል ዝግጁ ነን" ብለዋል፡፡
ሀወሃት ከውስጥና ከውጭ ጠላቶች ጋር አብሮ ሀገርን በማፍረስና ዜጎችን በመግደል ለሰላም ጠንቅ መሆኑን አሳይቷል ያሉት ደግሞ የመንግስት ሰራተኛው አቶ ታደሰ ዋቅቶላ ናቸው፡፡
"መንግስት ያወጀውን ሀገር የማዳን ጥሪ በመቀበል ለሰራዊቱ ደመወዝ ከመስጠት ባለፈ በየተሰማራንት መስክ ውጤታማ ሥራ ለመስራት ተዘጋጅተናል" ብለዋል፡፡
የጤና ባለሙያ የሆኑት አቶ አንተነህ ሽመልስ በበኩላቸው ደመወዛቸውን ከመለገስ ባለፈ ግንባር ድረስ በመዝመት ሠራዊቱ ለማገዝ ዝግጁነት እንዳላቸው ገልጸው፤ "እኛም ለሀገራችን ወታደር መሆናችንን እናስመሰክራለን" ሲሉ ገልጸዋል።
የባጃጅ አሽከርካሪ ወጣት አብዱልቀኒ አብዱልፈታህ፤ ህዝቡን በመከፋፈል ለ27 ዓመታት ጨቁኖ ሲገዛ የነበረው አሸባሪው ህወሃት በህዝብ አንድነት ከስልጣን መወገዱን አስታውሷል፡፡
አሁን ቡድኑን ለመደምሰስ በሚካሄደው ዘመቻ ላይ ለመሳተፍ መዘጋጀቱን ገልጾ፤ "በአሁኑ ወቅት የባጃጅ አሽከርካሪዎችና ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን የአካባቢያችንን ሰላም በአሸባሪው ተላላኪዎች እንዳይታወክ እየተቆጣጠርን ነው" ብሏል።
እድሜያቸው 85 ዓመት እንደሆነ የተናገሩት እማሆይ አየለች፤ "በእድሜዬ ብዙ ጠላቶች ተፈራርቀውብን አይተናል፤ እንደ አሁኑ ዓይነት ሀገርን የሚጠላና ህዝቡን ለስቃይ የዳረገ ጠላት አይቼ አላውቅም" ብለዋል።
"ይህ የሀገር ጠላት እንዲጠፋ ለሰራዊቱና ለሀገሬ ቀንና ሌሊት እየፀለይሁ ነው" ሲሉ ለሀገራቸው ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል፡፡
በተመሣሣይ ዕድሜ ላይ የሚገኙት አቶ ማሩ አምዴ "ለሀገርና ህዝብ ሲባል ወያኔን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መደምሰስ አለበት" ብለዋል፡፡
ለሰራዊቱ ስንቅ በማዘጋጀት ላይ ከሚገኙት መካከል ወይዘሮ ውባየሁ ወልዴ መንግስት ያቀረበው ሀገራዊ ጥሪ ተገቢና ትክክለኛ መሆኑን ተናግረዋል።
"ጦረኝነትን መፍትሄ ያደረገውን የሽብር ቡድኑን ማስወገድ ወሳኝ እርምጃ ነው፤ እኛ ለሰራዊቱ ስንቅ ማዘጋጀታችንን እንቀጥላለን፤ እስከመጨረሻው ድረስ ኃላፊነታችን እንወጣለን" ብለዋል፡፡