ቀጥታ፡

አንዳንድ አለምአቀፍ የሚዲያ አካላት ሃቅ ማዛባታቸውን አሁንም ቀጥለዋል

ነሐሴ 5 / 2013 (ኢዜአ) በትናንትናው እለት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ያስተላለፈውን ውሳኔ መሰረት በማድረግ አንዳንድ አለምአቀፍ የሚዲያ አካላት ሃቅ ማዛባታቸውን እንደቀጠሉ መሆናቸው የወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ አስታወቀ።

አሸባሪው ህወሃት እያደረሰ ያለውን ጥፋትና ሰቆቃ ለማስቆም ለ100 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን እና ለአለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ግልጽ ተደርጎ እንደተላለፈ እየታወቀ አንዳንድ የሚዲያ ተቋማት ግን መልእክቱን ያስተላለፉበት መንገድ የተዛባና ሆነ ተብሎ ባልተገባ መንገድ ተተርጉሞ የቀረበ መሆኑን ጠቁሟል።

አሸባሪው ህወሃት በአጎራባች የአፋርና የአማራ ክልል ንጹሃን ላይ ጭፍጨፋ ሲፈጽም አይተው እንዳላዩና ሰምተው እንዳልሰሙ ያለፉት የሚዲያ ተቋማቱ የህልውና ትግል ጥሪው ላይ የተዛባ ምስል ሊፈጥሩለት መሞከራቸውን ገልጿል።

“ተቋማቱ ያወጧቸው ርእሰ ዜናዎች አሸባሪው ህወሃት ያደረሳቸውን ጉዳቶች ሆነ ብለው ዘንግተዋቸዋል” ብሏል።

ትግራይ የሉአላዊት ኢትዮጵያ አንዷ ክፍል መሆኗ ግልጽ ሆኖ እያለ የትግራይ ሃይሎች የሚል ስያሜ በመስጠት የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ከመዳፈራቸውም በላይ ሁኔታውን በሁለት አገራት መካከል የሚደረግ ጦርነት የማስመሰል ተደጋጋሚ ሙከራና ኢትዮጵያውያንን የመከፋፈል ጥረቶች እንደነበሩ አስገንዝቧል።

ዜናዎቹ አሸባሪው ህወሃት በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ላይ ሲያደርስ የነበረውን ሰቆቃ ባለማንሳት የኢትዮጵያ መንግስትን በአጠቃላይና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን በግለሰብ ደረጃ በመኮነን ላይ ማተኮራቸውን ገልጿል።

በርካቶቹ ዘገባዎችም ተቆርጠው የተቀጠሉና እርስ በርስ የተቀባበሏቸው መሆናቸውን አሳውቋል።

ተቋማቱ የአሸባሪው ድርጅት አመራሮች መብረቃዊ ጥቃት ያሉትን እርምጃ አወድሰው መከላከያ ሃይሉ ላይ ጉዳት በማድረሳቸው የህግ ማስከበር ዘመቻው እንደተጀመረ ማስታወስ አለመፈለጋቸውን የገለፀው መረጃ ማጣሪያ፤ ኤኤፍፒ፣ ኤፒ እና ዋሽንግተን ፖስት በህገመንግስታዊ መንገድ ሽብርተኛ ለተባለው ድርጅት ከሙያዊ ስነምግባር ባፈነገጠ ሁኔታ ጥብቅና የቆሙበት ምክንያት ጥያቄ መፍጠሩን አንስቷል።

ከ100 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ያላት ኢትዮጵያ ያወጣቻቸውን ህግጋትና ሉአላዊነቷን ባለማክበር የሚደረጉት ሃቆችን የማዛባት ተግባራት ላለፉት ዘጠኝ ወራት ተጠናክረው መቀጠላቸውንም አስታውሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም