ሁላችንም ለሀገራችን ያለምንም ልዩነት ወታደር ነን! - ኢዜአ አማርኛ
ሁላችንም ለሀገራችን ያለምንም ልዩነት ወታደር ነን!
ባህር ዳር ፤ ነሐሴ 5/2013 (ኢዜአ) የተደቀነብንን የህልውና አደጋ ለማክሸፍ ሁላችንም ለሀገራችን ያለምንም ልዩነት ወታደር ነን!
በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ህዝባዊ የውይይት መድረክ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምሁር ዶክተር ቴዎድሮስ ኃይለማርያም በመድረኩ "ዘመቻ ህልውና ክተት፣ መክት ለፍትህና ነፃነት" በሚል ርዕስ የመወያያ ፅሑፍ አቅርበዋል።
በእዚህም ህዝቡ ከተደቀነበት የህልውና አደጋ ለመውጣት በአንድነት ተደራጅቶ ሊታገል፣ ሊመክትና ጠላትን በአጭር ጊዜ ድል ሊያደርግ እንደሚገባ ነው የተናገሩት።
አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን በማፍረስ አማራን ከምድረገፅ አጠፋለሁ ብሎ በአደባባይ ከማወጅ ባለፈ ህጻናትን ጭምር ለጦርነት አስገድዶ በማሰለፍ በህዝብ ላይ ግልፅ ጦርነትና ወረራ ፈጽሟል።
"የተደቀነውን የህልውና አደጋ ለማክሸፍና ይህን የጥፋት ሀይል መክቶ ለመደምሰስ ምሁሩን ጨምሮ ሁላችንም በኢትዮጵያዊ አንድነት መሰለፍ ይኖርበታል" ብለዋል።
"ለህልውና ዘመቻው ከእያንዳንዱ ሰው አስተዋጾ ይጠበቃል" ያሉት ዶክተር ቴዎድሮስ ፤ገንዘብ፣ ጉልበትና ህይወትን ጭምር መስዋዕትነት ለመክፈል ቆርጦ መነሳት እንደሚያስፈልግ ነው ያመለከቱት።
"ህወሓት ለ27 ዓመታት ሀገርን በበላይነት ሲመራ ዘርፎናል፤ ገድሎናል፤ የጅምላ ጭፍጨፋም በህዝባችን ላይ ፈፅሟል፤ ሀገሪቱንም አራቁቷል'' ብለዋል።
"ሁላችንም ለክልላችንና ለሀገራችን ያለምንም ልዩነት ወታደር ነን፤ ሊወረንና ሊበታትነን የመጣውን የጥፋት ኃይል መመከትና መደምሰስ ይገባናል" ሲሉም አክለዋል።
ህብረተሰቡ አካባቢውን ተደራጅቶ በንቃት ከመጠበቅ ባለፈ በግንባር ለሚፋለመው መከላከያ ሠራዊት የጀመረውን የሎጂስቲክ ድጋፍ እንዲያጠናክርም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ በበኩላቸው ፤ የመድረኩ ዓላማ በአሸባሪው ትህነግ የተከፈተውን ወረራ ህዝቡ በአግባቡ ተገንዝቦ እንዲመክት ለማነሳሳት መሆኑን ተናግረዋል።
በትህነግ የተከፈተብንን ጦርነት ለመመከት አቅም ያለው ሁሉ ወደ ግንባር በመዝመት ጠላትን ለመፋለም ከፍተኛ መነሳሳትና ቁርጠኝነቱን እያሳየ ነው።
ወደግንባር መሄድ የማይችለው ትጥቅና ስንቅ በማቀበልና አካባቢውን ከሰርጎ ገቦች ነቅቶ በመጠበቅ ደጀንነቱን እንዲያረጋግጥም ጥሪ አቅርበዋል።
ዶክተር ድረስ የመንግስት ሠራተኛው የወር ደመወዙን፤ የንግዱ ማህበረሰብ፣ ባለሃብቱና ሌላው ማህበረሰብም የድርሻውን በማዋጣት እገዛ በማድረግ ላይ ናቸው ብለዋል።
''አሸባሪ ህወሓት ለ27 ዓመታት ሀገርን በበላይነት ለማስተዳደር የቻለው አማራም ደግፎት ለቤተመንግስት ስላበቃው ነው'' ያሉት ደግሞ የውይይቱ ተሳታፊ አቶ እርስቱ አበበ ናቸው።
ቡድኑ ላለፉት ዓመታት በአማራው ላይ ሰይጣናዊ ግፍና በደል ማድረሱን አስታውሰው፤ "አሁን ወረራ የፈጸመው አማራን አንበርክኬ እገዛለሁ ብሎ አስቦ ከሆነ ምኞቱ አይሳካለትም" ብለዋል።
ትህነግ አማራ ክልል ላይ ተቀብሮ ይቀራል እንጂ የአማራ ህዝብ ዳግም ራሱን ለባርነት አሳልፎ ይሰጣል ብለው እንደማያምኑም ነው የገለጹት።
''ይህንን አሸባሪ ቡድን ለመፋለምና ከምድረገፅ ለማጥፋት እኔም ግንባር ቀደም ሆኜ ለመሰለፍ ዝግጁ ነኝ'' ሲሉም ተናግረዋል።
በውይይት መድረኩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ምሁራን፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።