አሸባሪውን ለመደምሰስ ለተጀመረው ሀገራዊ ዘመቻ ስኬታማነት ድጋፋችን ይቀጥላል- የድሬዳዋ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪውን ለመደምሰስ ለተጀመረው ሀገራዊ ዘመቻ ስኬታማነት ድጋፋችን ይቀጥላል- የድሬዳዋ ነዋሪዎች
ድሬዳዋ፤ ነሐሴ 5/2013 (ኢዜአ) አሸባሪውን የህውሃት ርዝራዥ ለመደምሰስ ለተጀመረው ሀገራዊ ዘመቻ ስኬታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጋችንን እንቀጥላለን ሲሉ የድሬዳዋ ነዋሪዎች አስታወቁ።
እናቶች ለሠራዊቱ ስንቅ ከማዘጋጀት ባሻገር ለሀገር ሰላምና ለኢትዮጵያ ጠላቶች መወገድ እየፀለዩ ነው።
ሀገራዊ ጥሪውን ተከትሎ ኢዜአ ያነጋገራቸው የድሬዳዋ ነዋሪዎች፤ ጦረኝነትን መፍትሄ ያደረገውን የሽብር ቡድኑን ማስወገድ ወሳኝ እርምጃ ነው፤ የአካባቢያቸውን ሰላም በአሸባሪው ተላላኪዎች እንዳይታወክ እየተቆጣጠሩ ይገኛሉ፡፡
መሠረት ማኔ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጭምር በማሰልጠንና የወንድ እግር ኳስ ክለብ በማሰልጠን በአፍሪካ የመጀመሪያዋ ሴት ሲሆኑ ሠራዊቱ ሀገርን ለማፍረስ የሚጣጣረውን የአሸባሪው ርዝራዥ ለመደምሰስ የጀመረውን ተልዕኮ ለማሳካት አስፈላጊውን ድጋፍ አደርጋለሁ ብለዋል ፡፡
ለሀገር ሰላም፣ ለትግራይ ህዝብ ደህንትና ልማት መረጋገጥ መንግስት የሰጠውን ዕድል በመናቅ ህውሃት ህጻናትን ለጦርነት መማገዱ የሚወገዝ ተግባር ነው፡፡
ይህም ቡድኑ ሀገር የማፍረስ ተልዕኮ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይና አለም አቀፍ መንግስታት ጭምር ሊያወግዙት የሚገባ ወንጀል ነው ብለዋል፡፡
ቡድን በመደምሰስ ተግባር ሁላችንም ባለን ጉልበት፤ ዕውቀት፣ ገንዘብ ከሠራዊቱ ጎን እንቆማለን ነው ያሉት።
የቀድሞ የአየር ኃይል ሠራዊት አባል አቶ ግርማ ትቶኝ፤ የሀገርንና የትግራይን ህዝብ እየጠበቀ የነበረውን የመከላከያ ሠራዊት ላይ ህውሃት የፈፀመው ጥቃት የሀገር ከሃዲነቱን የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ይህንን ባንዳ ለመደምሰስ የቀድሞ ሠራዊት፣ የአየር ኃይል አባላት አስፈላጊውን መስዋትነት ለመክፍል ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡
ሀወሃት ከውስጥና ውጭ ጠላቶች ጋር አብሮ ሀገርን በማፍረስና ዜጎችን በመግደል ለሰላም ጠንቅ መሆኑን አሳይቷል ያሉት ደግሞ የመንግስት ሰራተኛው አቶ ታደሰ ዋቅቶላ ናቸው፡፡
መንግስት ያወጀውን ሀገር የማዳን ጥሪ በመቀበል ለሰራዊቱ ደመወዜን ከመስጠት ባለፈ በየተሰማራንት መስክ ውጤታማ ሥራ ለመስራት ተዘጋጅተናል ብለዋል፡፡
የጤና ባለሙያ አቶ አንተነህ ሽመልስ በበኩላቸው፤ የድሬዳዋ ጤና ባለሙያዎች ግንባር ድረስ በመዝመት ሠራዊቱ ለማገዝ ዝግጁ ነን፤ እኛም ለሀገራችን ወታደር መሆናችንን እናስመሰክራለን ሲሉ በላቀ የሀገር ፍቅር ስሜት ድጋፋቸውን ገልጸዋል።
ከዚህ ባሻገር ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ደመወዛቸውን በመለገስ ጭምር ሀገራዊ ዘመቻው እንዲሳካ ኃላፊነታችን እንወጣለን ብለዋል፡፡
የባለሶስት እግር ታክሲ አሽከርካሪ ወጣት አብዱልቀኒ አብዱልፈታህ፤ ህወሃት ህዝቡን በመከፋፈል ለ27 ዓመታት ጨቁኖ ቢገዛም ህዝቡ በአንድነት ከስልጣን ማስወገዱን አስታውሷል፡፡
አሁን የቀረው ርዝራዥ ለመደምሰስ በሚካሄደው ዘመቻ ላይ በመሳተፍ እኔም ሆንኩ የስራ ባልደረቦቼ ዝግጁ ነን ብሏል፡፡
በተለይ እኛ ወጣት አሽከርካሪዎች ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን የአካባቢያችንን ሰላም በአሸባሪው ተላላኪዎች እንዳይታወክ እየተቆጣጠርን እንገኛለን ነው ያለው፡፡
እድሜያቸው 85 ዓመት እንደሆኑ የተናገሩት እማሆይ አየለች፤ በእድሜዬ ብዙ ጠላቶች ተፈራርቀውብን አይተናል ፤ እንደ አሁኑ ዓይነት ሀገርን የሚጠላና ህዝቡን ለስቃይ የዳረገ ጠላት አይቼ አላውቅም ብለዋል።
ይህ የሀገር ጠላት ወያኔ እንዲጠፋ ምንም ማድረግ ባልችል ለሰራዊቱና ለሀገሬ ቀንና ሌሊት እየፀለይሁ ነው ሲሉ ለሀገራቸው ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል፡፡
በተመሣሣይ ዕድሜ ላይ የሚገኙት አቶ ማሩ አምዴ በበኩላቸው፤መደራደር አያስፈልግም፤ ለሀገርና ህዝብ ሲባል ወያኔን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መደምሰስ አለበት ብለዋል፡፡
ሠራዊቱን እኛ በፀሎት፣ ወጣቱ ደግሞ በጉልበቱና በመዝመት ሀገራችን ጠብቀን ማቆየት አለብን በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ለሰራዊቱ ስንቅ በማዘጋጀት ላይ ከሚገኙት የድሬዳዋ ሳቢያን ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ውባየሁ ወልዴ መንግስት ያቀረበው ሀገራዊ ጥሪ አዋጁ ተገቢና ትክክለኛ መሆኑን ተናግረዋል።
ጦረኝነትን መፍትሄ ያደረገውን የሽብር ቡድኑን ማስወገድ ወሳኝ እርምጃ ነው፤ እኛ ለሰራዊቱ ስንቅ ማዘጋጀታችንን እንቀጥላለን ፤ እስከመጨረሻው ድረስ ኃላፊነታችን እንወጣለን ብለዋል፡፡