አሸባሪው ሕወሃት የትግራይን ህዝብ እንዲነጠል ለማድረግ እየሄደበት ያለው እኩይ ሴራ ተቀባይነት የለውም - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ሕወሃት የትግራይን ህዝብ እንዲነጠል ለማድረግ እየሄደበት ያለው እኩይ ሴራ ተቀባይነት የለውም
አዲስ አበባ ነሃሴ 05/2013(ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት የትግራይን ህዝብ እንዲነጠል ለማድረግ እየሄደበት ያለው እኩይ ሴራ ተቀባይነት የለውም ሲል የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ትዴፓ/ አስታወቀ፡፡
የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር በመሆን "የአሸባሪውን ህወሃት ግብዓተ መሬት ማፋጠን አለበት" በማለት ነው ትዴፓ የገለጸው።
አሸባሪው ሕወሃት በትግራይ "ንጉስ" ሆኖ ለመቆየት ሲል ህዝቡን ለመነጠል እያሴረ መሆኑንም ተጠቁሟል።
የትዴፓ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሙሉብርሃን ኃይሌ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
በቆይታቸውም አሸባሪው ቡድን የትግራይን ህዝብ ከኢትዮጵያ የመነጠል ድብቅና እኩይ ሴራ እንዳለው ይፋ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
ይህም የሽብር ቡድኑ እንደሚለው ሳይሆን የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ህግ ማስከበር ሂደቱ የገባው የአሸባሪው ቡድን ሰሜን ዕዝ ላይ በደረሰው ድንገተኛ ጥቃት ተገዶ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
መንግስት በትግራይ ቆይታውም የትግራይን ህዝብ ማረጋጋት፣ ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረስና የፈረሱ የመሰረተ ልማቶችን ሲያከናውን መቆየቱንም ገልጸዋል፡፡
መንግስት ይህን ያደረገውም "የትግራይ ክልል የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት" በመሆኗ ነው በማለት ገልጿል።
እንደ ሃላፊው ገለጻም "የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ወገኖች ጋር በመሆን ኢትዮጵያን የገነባ" በመሆኑ ከኢትዮጵያኖች ወገኖቹ የመለየት ሃሳብ የሌለው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ይህ የአሸባሪ ቡድን ግን የትግራይን ህዝብ ከኢትዮጵያኖች በመነጠል በክልሉ"ንጉስ" ሆኖ የመቆየት ህልም እንዳለውም አብራርተዋል፡፡
በዚህም በለመደው መልኩ ህዝቡን የመዝረፍ፣ የማወናበድና የመበደል እኩይ ዓላማና ፍላጎት እንዳለውም ገልጸዋል፡፡
የትግራይ ህዝብ መቼም ቢሆን በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራና ከሌሎች ወገኖች ጋር በመሆን ለዕድገቷም የሚተጋ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
"አሸባሪው ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ የትግራይን እናት ልጅ ሲያስፈጅ የኖረ ነው" ያሉት ሃላፊው፤ አሁንም ከዚህ ድርጊቱ ሳይቆጠብ ህጻናትን ለጦርነት በመማገድ ላይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ ወደ ጦርነት አልሄድም ያለውንም ሰው እያንገላታና እየገደለ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ለዚህ ሽብር ቡድን መጥፋትም የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር በመሆን ግበዓተ መሬቱን ማፋጠን እንደሚኖርበት ነው የተናገሩት።
መንግስት በትግራይ ክልል አርሶ አደሩ የክረምቱን ወቅት የእርሻ ስራውን እንዲያከናውን እና የሰብዓዊ ድጋፍ ባልተገደበ መልኩ እንዲገባ የተናጠል የተኩስ አቁም በማድረግ ከትግራይ ለቆ መውጣቱ ይታወሳል፡፡
አሸባሪው ቡድን ግን የተኩስ አቁሙን ባለመቀበል የተለያዩ በአጎራባች ክልሎች ትንኮሳዎችን ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
አሸባሪው ህወሓት በአፋር ጋሊኮማ በትምህርት ቤት እና በጤና ጣቢያ ተጠልለው በነበሩ ዜጎች በከባድ መሳሪያ በፈጸመው ጥቃት ከ200 በላይ ሰዎችን ገድሏል። ከዚህ ውስጥ 107ቱ ህጻናት መሆናቸውን አልጀዚራ ማጋለጡ ይተወሳል።
በትናንትናው ዕለት መከላከያ ሰራዊት እና የክልል ልዩ ኃይሎች ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የተነሳውን የክህደት ኃይል ለመደምሰስ ብርቱና የማያዳግም ክንዳቸውን እንዲያሳርፉ አቅጣጫ መሰጠቱ ይታወቃል፡፡