ቀጥታ፡

የአሸባሪውን ቡድን ሃገር የማፍረስ ሴራ በአጭር ለመቋጨት ብርቱ ጥረት እየተደረገ ነው

ደሴ ፤ ነሐሴ 5/2013(ኢዜአ) የህውሃት አሸባሪ ቡድን አማራን በማዳከም ኢትዮጵያ  ለማፈራረስ እየፈፀመ ያለውን ወረራና ግፍ በአጭር ጊዜ ለመቋጨት ብርቱ ጥረት እያደረገ መሆኑን የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በአማራ ክልል በሚገኝ ማሰልጠኛ ተቋም የሰለጠኑ  ሁለገብ የፀጥታ ሃይል አባላት የምረቃ ስነ-ስርዓት እየተካሄደ ነው።

በምረቃ ስነ-ስርዓት የጽህፈት ቤቱ ምክትል ሃላፊ አቶ ጎሹ ስንቴ እንዳስታወቁት፤ ሰልጣኞች ከምስራቅ አማራ የተለያዩ ዞኖች የተውጣጡ ናቸው።

ሰልጣኞቹ አሸባሪውን ቡድን ለመደምሰስ የሚያስችል መሰረታዊ የወታደራዊ ስልጠና ወስደው ብቁ በመሆናቸው ለዛሬ ምረቃ በቅተዋል ብለዋል።

የአሸባሪ ቡድኑ አማራን በማዳከም ኢትዮጵያ ለማፈራረስ የወጠነውን ሴራ ለማክሸፍ ሰልጣኞቹ ጉልህ ሚና እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።

በክልሉ እያደረሰ ያለውን ወረራና የሚፈፅመውን ግፍ በአጭር ጊዜ ለመቋጨት የክልሉ መንግስት ብርቱ ጥረት እያደረገ ነው።

የመንግስትን የክተት ጥሪ ተቀብለው በሌሎች አካባቢዎችም መሰል ስልጠናዎች እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፤ ተመራቂዎቹ ቀጥታ ወደ ግንባር በመሄድ አሸባሪውን የህወሃት ቡድን ይፋለማሉ ብለዋል።

ከሰልጣኞች መካከልም ወደ መከላከያ የሚቀላቀሉ እንዳሉ አመልክተው፤የኢትዮጵያ  ህዝብ አንድነቱን ጠብቆ አሸባሪውን ቡድን ለመደምሰስ የጀመረውን የህልውና ትግል አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅረበዋል።

በምረቃ ስነ- ስርዓቱ የክልል፣ ዞንና  ደሴ ከተማ አስተዳደር አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም