ቀጥታ፡

በአልጀሪያ በተከሰተ የሰደድ እሳት የ 42 ሰዎች ህይዎት አለፈ

ነሃሴ 5-2013 (ኢዜአ) በአልጄሪያ ዋና ከተማ አልጄርስ በስተምስራቅ በኩል ካቢሊ በተባለ ቦታ በደረሰው የሰደድ እሳት አደጋ 42 አልጀሪያዊያን መሞታቸውን የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አስታውዋል።

የሞት አደጋው ያጋጠመው ሰሞኑን በአልጀሪያ ዋና ከተማ ከአልጀርስ በስተምስራቅ በኩል በምትገኝ ካቢሊ በተባለው ስፍራ የተከሰተውን የሰደድ እሳት ለማጥፋት በርብርብ ላይ በነበሩ ዜጎች ላይ ነው፡፡

ከሟቾች መካከል 25 የሚሆኑት ወታደሮች ሲሆኑ ቀሪዎቹ 17ቱ ደግሞ ሲቪሎች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ከሰደድ እሳቱ አደጋ ከ 100 በላይ ሰዎችን ማዳን መቻሉም ተገልጿል።የሰደድ እሳቱ መነሻ ምክንያትም በአሁኑ ሰዓት በአለም ላይ እየጨመረ የመጣው የሙቀት መጠን ነው ተብሏል፡፡በቅርቡ በበርካታ የሜዲትራኒያን አገሮች ማለትም በቱርክ ፣ ግሪክ ፣ ሊባኖስ እና ቆጵሮስን ጨምሮ የእሳት አደጋ መከሰቱ ይታወሳል።

ከኢንዱስትሪ ዘመን ጀምሮ የአለም የሙቀት መጠን እየጨመረ የመጣ ሲሆን ይህም የሰደድ እሳት መከሰትን እያባባሰ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ይህም በሰው፤ በእንስሳት እና እጽዋት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ለዚህም በዓለም ዙሪያ ያሉ መንግስታት ወደ አየር የሚለቀቀውን የበካይ ጋዝ ልቀት ቅነሳ ካላደረጉ የሙቀት መጠኑ አሳሳቢ ሆኖ እንደሚቀጥል ተዘግቧል፡፡

በአሁኑ ሰዓትም በ 17 የአልጄሪያ አውራጃዎች ከ 100 በላይ ቃጠሎዎች መከሰታቸውን የሀገሪቱ የዜና ወኪል ትላንት ማታ ዘግቧል፡፡በተመሳሳይ የአልጄሪያ ጎረቤት የሆነችው ቱኒዚያም በሀገሯ ክብረወሰን የሆነ ሙቀት መመዝገቡን አስታውቃለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም