የደብረብርሀን ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የወር ደመወዛቸውን ለመስጠት ወሰኑ - ኢዜአ አማርኛ
የደብረብርሀን ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የወር ደመወዛቸውን ለመስጠት ወሰኑ
ደብረብርሀን ፤ ነሐሴ 05/2013 (ኢዜአ) የደብረብርሀን ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ በህልውና ዘመቻው በግንባር ላይ ለሚዋደቀው ለመከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የፀጥታ ሃይሎች የወር ደመወዛቸውን ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ ለመስጠት ወሰኑ።
የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ በደብረ ብርሃን ከተማ ውይይት በማካሄድ ደመወዛቸውን ለመስጠት ከወሰናቸውም በተጨማሪ ለሰራዊቱ ደም ለግሰዋል።
በውይይት መድረኩ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ንጉስ ታደሰ ፤መላው ህዝብ ተባብሮ ከመንግስት ጎን በመሰለፍ ሀገርን ለማፍረስ የመጣውን ጠላት መመከት ያለበት ወቅት ላይ እንገኛል ብለዋል።
በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ፣ የዜጎች ነፃነትና ክብር እንዲጠበቅ ሀገር አፍራሹን የህውሃት ቡድን ለማስወገድ በተደረገው የህግ ማስከበር ዘመቻ የተቋሙ ማህበረሰብ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ዛሬም በሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ በመወያየት መላ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በ11 ወር ተከፍሎ የሚጠናቀቅ የአንድ ወር ደመወዛቸውን በአንድ ድምጽ መወሰናቸውን አሰታውቀዋል።
በተጨማሪም በደም ልገሳ መርሀ ግብር መሳተፋቸውን ጠቁመው በግንባር ተገኝተውም በስንቅ ማቀበል፣ ቁስለኛን በመንከባከብ እና የዘማች ቤተሰቦችን ለመደገፍ ጥያቄ አቅርበዋል።
በውይይቱ ከተሳተፉ የተቋሙ ማህበረሰብ አባላት መካከል አቶ ብርሃን አባቢ፤ የሀገር መከለላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ሀይል፣ ሚኒሻና ፋኖ ለሀገር ከሚከፍሉት ዋጋ አንፃር የሚደረገው ድጋፍ ዝቅተኛ ነው ብለዋል።
የአሸባሪውን ቡድን በመደምሰስ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚደረገው የህልውና ዘመቻ አካል በመሆን ጦር ግንባር ድረስ ዘልቀው ከሰራዊቱ ጎን ለመሰላፍ መወሰናቸውንም አስታውቀዋል።
የዩኒቨርሲቲው መምህር ዶክተር ሊድያ ጫንያለው በበኩላቸው፤ የደገፍነው የወር ደመወዝ በቂ ባለመሆኑ በቀጣይ በቁሳቁስ፣ በሙያቸውና ግንባር ድረስ በመሰለፍ ለመደገፍ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
የጀመሩትን ድጋፍ በቀጣይ በሚያስፈልገው ሁሉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አረጋግጠዋል።
ድጋፉን ያደረጉት ከ2ሸህ 500 በላይ የደብረብርሀን ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ሰራተኞችና መምህራን መሆናቸው ተመልክቷል።