የሚኒስቴሩ ሠራተኞች ለአገር መከለከያ ሠራዊት ድጋፍ የአንድ ወር ደመወዛቸውን ሰጡ - ኢዜአ አማርኛ
የሚኒስቴሩ ሠራተኞች ለአገር መከለከያ ሠራዊት ድጋፍ የአንድ ወር ደመወዛቸውን ሰጡ
አዲስ አበባ፤ ነሀሴ 04 ቀን 2013 (ኢዜአ) የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሠራተኞችና የአመራር አባላት ለአገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ እንዲውል የአንድ ወር ደመወዛቸውን ሰጡ።
ሠራተኞቹ "ከአገር መከላከያ ሠራዊት ጎን ለመሰለፍ ዝግጁ ነን" በማለት ደም የለገሱ ሲሆን ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የአካል ድጋፍ ቁሳቁስም አስረክበዋል።
የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ የሠራዊቱ አባላት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማረጋገጥና ዳር ድንበሯን ለማስጠበቅ ሕይወታቸውን መስዋዕት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
የውጭና የውስጥ አፍራሽ ሃይሎች ኢትዮጵያን በማፍረስ እንደ አገር እንዳትቀጥል ለማድረግ እየጣሩ መሆኑን በመግለጽ ሠራዊቱ ይህን ሴራ ለማክሸፍ በሚያደርገው ተጋድሎ ሕዝቡ ከጎኑ እንዲቆም ጠይቀዋል።
የሚኒስቴሩ ሠራተኞች ለመከላከያ ሠራዊት የአንድ ወር ደመወዛቸውን የሰጡ ሲሆን ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የተለያዩ የአካል ድጋፍ መሳሪያዎችም አበርክተዋል።
ከአካል ድጋፍ መሳሪያዎቹ 30 ዊልቸር፣100 ክራንች፣ 45 መረማመጃና 20 መደገፊያዎች ይገኙበታል።
አመራሮችና ሠራተኞቹ በቀጣይም ለሠራዊቱ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ሚኒስትሯ አረጋግጠዋል።
የሚኒስቴሩ ሠራተኛ አቶ ደመቀ ገዛኸኝ ለሠራዊቱ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ጌታቸው ሃይለማሪያም የተቋሙ የስራ ሀላፊዎችና ሠራተኞች ለሠራዊቱ ላበረከቱት ድጋፍ ምስጋና በማቅረብ ይኸው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የመንግስት ተቋማት፣ ክልሎችና ከተማ አስተዳሮች፣ ባለሀብቶችና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች ለአገር መከላከያ ሠራዊት የገንዘብና የአይነት ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
በርካቶችም "ኢትዮጵያን ለማዳን እዘምታለሁ" የትም፣ መቼም፣ በምንም በሚል ለቀረበው አገራዊ ጥሪ ምላሽ በመስጠት የመከላከያ ሠራዊቱን እየተቀላቀሉ ነው።