የሀገርን ሉአላዊነት ለማስከበር ከመከላከያ ሠራዊት ጎን እንቆማለን - ኢዜአ አማርኛ
የሀገርን ሉአላዊነት ለማስከበር ከመከላከያ ሠራዊት ጎን እንቆማለን
ዲላ ፤ ነሐሴ 4/2013 (ኢዜአ) የሀገር ሉዓላዊነት ለማስከበር የሕይወት መስዋዕትነት እየከፈለ ካለው የመከላከያ ሠራዊት ጎን እንቆማለን ሲሉ የጌዴኦ ዞን ነዋሪዎች አሰታወቁ።
"ደሜን ለኢትዮጵያ" መሪ ሀሳብ የአንድ ሳምንት የደም ልገሳ ዘመቻ በዲላ ከተማ የተጀመረ ሲሆን በመጀመሪያው ቀን ብቻ ከ60 ዩኒት በላይ ደም መሰብሰብ ተችሏል።
ኢዜአ ካነጋገራቸው ደም ለጋሾች መካከል ወጣት ተገኝ ከፍያለው ፤የአሸባሪው ትህነግን ጥቃት ከሚመክተው መከላከያ ሠራዊት ጎን መሰለፍ የዜግነት ግዴታ ነው ይላል።
ከደም ልገሳው በተጨማሪ ወደ ግንባር ለመዝመት ዝግጁ እንደሆነ ነው ያስታወቀው።
"ደሜን ለሀገር መከላከያ ሠራዊት በመለገሴ ኩራት ይሰማኛል" ያሉት ደግሞ አቶ ባይከዳኝ ተስፋዬ ናቸው።
አሸበሪው ቡድን ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ግንባር ፈጥሮ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የያዘው ውጥን ለማክሸፍ ከመከላከያ ሰራዊት ጎን እቆማለሁ ብለዋል።
ሕይወቱን መስዋዕት አድርጎ ለሀገር ሉዓላዊነትና ክብር እየታገለ ያለው መከላከያ ሠራዊት በሚያስፈልገው ሁሉ ከጎኑ ልንቆም ይገባል ነው ያሉት።
የደም ልገሳው መርሃ ግብር አስተባባሪ የጌዴኦ ዞን ወጣቶች ሊግ ሃላፊ ወጣት ደግነት ሃይሉ፤ የዞኑ ሕዝብ በፈቃደኝነት ደሙን በመለገስ ለመከላከያ ሠራዊት ያለውን አጋርነት እያሳየ እንደሚገኝ ተናግሯል።
ለአንድ ሳምንት በሚቆየው የደም ልገሳ መርሃ ግብር 500 ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዷል።
ከደም ልገሳ ጎን ለጎን የሀብት ማሰባሰብና የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር እንደሚካሄድም ነው የተገለጸው።
የዲላ ደም ባንክ ሃላፊ ሲስተር መስተዋት ዘውዴ ፤ በዘመቻው የመጀመሪያ ቀን 60 ዩኒት ደም መሰብሰቡን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ አሸባሪው የትህነግ ቡድን የከፈተውን ጦርነት ለመመከት የሀገር መከላከያ ሠራዊትን በሰው ሃይል፣ገንዘብና ስንቅ በማዘጋጀት ድጋፍ እያደረገ ነው።