የአሸባሪውን ቡድን የሐሰት ፕሮፖጋንዳ አራጋቢዎች ሴራ በማክሸፍ በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ የድርሻውን አበርክቷል - ኢዜአ አማርኛ
የአሸባሪውን ቡድን የሐሰት ፕሮፖጋንዳ አራጋቢዎች ሴራ በማክሸፍ በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ የድርሻውን አበርክቷል
ነሀሴ 4/2013 (ኢዜአ) አሸባሪው የህወሓት ቡድን በሐሰተኛ መረጃ የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ እጁን እንዲያስገባ ያደረገውን ሙከራ በማክሸፍ የድርሻውን ማበርከቱን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የሠላም ጓድ ልዑክ ገለጸ።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የሠላም ጓድ ልዑክ በኢትዮጵያ በቆየባቸው ዘጠኝ ወራት በዜጎች ዘንድ መተማመንና መተባበር እንዲፈጠር ያደረገውን እንቅስቃሴ አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።
በመግለጫው የልዑኩ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር ብሩክ ሀይሉ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የሠላም ጓዱ የተቋቋመባቸውን ዓላማዎች በዝርዝር አስረድተዋል።
ፕሮፌሰሩ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ባሰማራቸው ቅጥረኞች ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ትክክለኛ መረጃ እንዳይኖረው በማድረግ ተግባር መጠመዱንም ገልጸዋል።
በተሳሳተ መረጃውም ኢትዮጵያ ደካማ አገር እንደሆነች በማስመሰል ጉዳዩ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ድረስ እንዲሄድ ማደረጉንም አውስተዋል።
ይሁንና በገንዘብ ባሰማራቸው ቅጥረኞች አማካኝነት የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ እንዲገባ ያደረጉት ሙከራ መክሸፉን ተናግረዋል።
የአሸባሪው ቡድን የሃሰት ፕሮፖጋንዳ አራጋቢዎችን ሴራ በማክሸፉ ተግባር በውጭ ያለው አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊና የዳያስፖራው የሠላም ጓድ የድርሻቸውን መወጣታቸውንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የሠላም ጓድ ዘላቂ ሠላም ለማስፈን፣ ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋምና ብሄራዊ ግዴታ የሆነውን የአገር ህልውና ለማስጠበቅ ከመንግስት፣ ከሕዝብና ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር ይሰራል ብለዋል።
የሠላም ጓዱ ልዑክ አባል አቶ አቤል ጋሼ አሸባሪው ቡድን በመከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያስተጋባውን ሐሰተኛ መረጃ ለመቀልበስ ተቸግረው እንደነበር አስታውሰዋል።
በተለይም ጥቃቱን ከፈፀመ በኋላ በነበሩት ጥቂት ወራት የተደራጀ ዝግጅት ስላልነበረን በውጭ አገራት በበርካታ ገንዘብ የገዛቸው ቅጥረኞች ብዙዎችን አሳስተዋል ብለዋል።
'አሁን ከዚያ ብዙ ተምረናል' ያሉት አቶ አቤል በቀጣይ ምን መስራት እንዳለብን ለይተናል፤ ተደራጅተን በመመከትም አገራችን ካጋጠማት የህልውና አደጋ እንድትወጣ የበኩላችንን እናደርጋለን ሲሉ ተናግረዋል።