ቀጥታ፡

ለአሸባሪው ህውሓት ለአፍታም ቢሆን የምንሰጠው ጊዜ አይኖርም ­- ሜ/ጀ መሠለ መሠረት

ነሐሴ 04 ቀን 2013 (ኢዜአ) “ለአሸባሪው ህውሓት ለአፍታም ቢሆን የምንሰጠው ጊዜ አይኖርም” ሲሉ የምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሜ/ጀ መሠለ መሠረት ተናገሩ፡፡

ሜ/ጀ መሰለ በዕዙ ውስጥ የሚገኘውን 314ኛ ኮር 31ኛ አድዋ ክፍለ ጦር እና 54ኛ ክፍለ ጦር የሠራዊት አባላት እየወሰዱ ያሉትን ስልጠና እና ወትሮ ዝግጁነት ተመልክተዋል።

በወቅቱም “አሸባሪውን የህውሓት ቡድን ላለፉት 27 ዓመታት የተሸከምንበት ጀርባችን ተልጧል ከአሁን በኃላ በህይወት እንዲኖር አንፈቅድለትም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አሸባሪው ህውሓትን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እየተቃወመው መሆኑ ሠራዊቱ ግዳጁን በአጭር ጊዜ እንዲያጠናቅቅ ስንቅ እንደሚሆነውም ገልጸዋል።

አሸባሪው የህውሓት ቡድን ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ እያለ ፕሮፖጋንዳ እያሰራጨ መሆኑን ገልጸው፤ ቡድኑ ኢትዮጵያን ማፍረስ ቀርቶ ራሱን ማደራጀት የማይችል መሆኑን ተናግረዋል።

“አሁን እየወሰዳችሁት ያለው ስልጠና አሸባሪውን የህውሓት ቡድንን በአጭር ጊዜ መደምሰስ የሚያስችል እና ጁንታው ዳግም በኢትዮጵያ ምድር እንዳይታይ የሚያደርግ ነው” ሲሉም መናገራቸውን የአገር መከላከያ ሰራዊት በመረጃው አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም