ኢትዮጵያ የምዕራባዊያን ፍላጎት ባለመቀበል የያዘችው ቆራጥ አቋሙ በማፅናት መቀጠል ይኖርባታል

ጂንካ ፤ ነሐሴ 4/2013 (ኢዜአ) ምዕራባውያን በተለያዩ አገራት ላይ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ተላላኪ መንግስት ስለሚፈልጉ ኢትዮጵያ ይህንን ባለመቀበል የያዘችውን ቆራጥ አቋሙ በማፅናት መቀጠል ይኖርባታል ሲሉ ምሁራን ተናገሩ።
ኢትዮጵያዊያን በውጪና ውስጥ ሀይሎች የተሸረበብንን የጥፋት ሴራ ተገንዝበን ለማክሸፍ ከመንግስት ጎን መሰለፋችን ጠላቶቻችንን አሳፍሯል።

የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ አሸባሪው ህወሓት  ሀገር ለማፍረስ  የከፈተውን ጦርነት   ሕብረትን በማጠናከር መመከት ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው።

በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ኤልያስ አለሙ፤  ምዕራባዊያን ፍላጎታቸውን ለማሳካት በሚፈልጉባቸው ሀገራት ደካማና እንደተፈለገው የሚጠመዘዝ ተላላኪ መንግስት ለማኖር አበክረው እንደሚሰሩ አስረድተዋል።

እንደ ኢራቅ፣ ሶሪያ፣ የመን፣ ሊቢያና መሰል ሀገራት በሰብዓዊ መብት ጥሰት እና በእርዳታ ሰበብ ፍላጎታቸውን ሲያስፈፅሙ መታየታቸውንም አስታውሰዋል።

በእነዚህ ሀገራት እስከዛሬ ድረስ የማያባራ ጦርነት እንዲኖር በማድረግ ሀገራቱን ማፈራረሳቸውንም ነው ዶክተር ኤልያስ ያመለከቱት።

"ይህንንም ድብቅ ሴራቸውን ለማስፈፀም ባደራጇቸው ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም 'በሬ ወለደ' ዓይነት የፈጠራ ወሬዎችን በማስተጋባት ዓለምን በማሰመን ሴራቸውን ሲያስፈፅሙ ቆይተዋል" ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተው ዘመቻም ይህንኑ ፍላጎታቸውን ለማሳካት አስበው ነው።

"በሱዳን በኩል ያለው መተላለፊያ ኮሪደር ይከፈት፤ ከሽብርተኛው ህወሓት ጋር ተደራደሩ፤ የሰበዓዊ መብት ስለተጣሰ ማዕቀብ ልንጥል ነው ዓይነት መሰል ማስፈራሪያዎች የመንግስትን አቅም በማዳከም ሀገር ለማፈራረስ የተሸረቡ ሴራዎች ናቸው" ብለዋል።

ዶክተር ኤሊያስ ፤ እነዚህን ሴራዎች ለማምከን መንግስት የያዘውን ቆራጥ አቋም ማጽናት ይኖርበታል ነው ያሉት።

በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን የሚስተጋባውን የሀሰት ወሬ ፈር ለማስያዝም የዲፕሎማሲ ስራዎች ተጠናክረው መጠቀል እንደሚኖርበትም አመላክተዋል።

በዩኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት ክፍል ሀላፊ መምህር ተሻለ ሻምበል በበኩላቸው "ኢትዮጵያዊያን በውጪና ውስጥ ሀይሎች የተሸረበብንን የጥፋት ሴራ ተገንዝበው ለማክሸፍ  ከመንግስት ጎን መሰለፋችን ጠላቶቻችንን አሳፍሯል" ብለዋል።

የሰበዓዊ መብት ተሟጋቾች ሳይቀሩ ህወሓት ለ27 ዓመታት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈፅም በቅርቡ ደግሞ በማይካድራ ንፁሃንን ሲጨፈጭፍና ህፃናትን ወደ ጦርነት ሲማግድ ከፍተኛ ወንጀል መሆኑን እያወቁ እንዳላወቁ መሆናቸውን አመልክተዋል።

"ይህም ድብቅ ዓላማቸውን ከማስፈፀም በቀር ለኢትዮጵያዊያን እንደማይጨነቁ ያሳያል” ብለዋል የህግ መምህሩ፡፡

አውቆ የተኛ ቢቀሰቅሱት አይሰማም እንዲሉ ከምዕራባዊያን ፍትሃዊ ውሳኔ መጠበቅ እንደማይገባና መንግስት በአቋሙ መጽናት አለበት ብለዋል።

"ትግሉ ከህወሓት የሽበር ቡድን ጋር ብቻ ሳይሆን ከውጭ ጠላቶቻችንም ጋር ነው" ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የስነ-ምግባርና የስነ-ዜጋ ትምህርት ክፍል ሀላፊ መምህር አንዷለም ግርማ ናቸው።

"የማህበረሰብ አንቂዎችም ሆኑ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች የሀገርን ህልውና የሚጎዱ ተግባራትን በማህበራዊ ሚዲያዎች ከማጋራት ሊጠበቁ ይገባል"  ብለዋል፡፡

እየተካሄደ ያለው የህልውና ዘመቻ ሀገር የማዳን በመሆኑ ሁላችንም የትኛውም ልዩነታችንን ወደጎን በመተው ከመንግስት ጎን ሆነን በሀገር የማዳን ሥራው ላይ መረባረብ ይጠበቅብናል።

የተቋሙ  የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሀይረዲን ሙሐመድ ፤ በማህበራዊ ትስስር ገፆች በሚሰራጩ ሀሰተኛ ወሬዎች ህዝቡ ሊሸበር እንደሚይገባ ተናግረዋል።

ሀሰተኛ ወሬዎች ህዝቡን ለማሸበርና በመንግስት ላይ እምነት እንዲያጣ ለማድረግ ሆን ተብለው የሚለቀቁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ይህንን በመገንዘብ የማህበራዊ ትስስር ገፆች ተጠቃሚዎች መረጃውን ከማጋራታቸው በፊት እውነታነቱ ከታማኝ   ምንጮች ማጣራት እንዳለባቸው መክረዋል።

መንግስትም ተገቢውን መረጃ በወቅቱ ለህዝብ በመስጠት ሀገር የማዳን ሥራውን አጠናክሮ  እንዲቀጥልም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም