የዳያስፖራው የሠላም ጓድ በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣውን የህልውና አደጋ ለመመከት ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
የዳያስፖራው የሠላም ጓድ በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣውን የህልውና አደጋ ለመመከት ይሰራል
አዲስ አበባ ነሀሴ 04/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የሠላም ጓድ በአገሪቷ ላይ የተቃጣውን የህልውና አደጋ ለመመከትና በውስጥና በውጪም ያለው ሕዝብ በአንድነት በመቆም እንዲከላከል እንደ ድልድይ ሆኖ እንደሚሰራ ገለጸ።
በተለያዩ አካላት ተሳትፎ የተመሰረተው የዳያስፖራ የሠላም ጓድ የኢትዮጵያ ቆይታውን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የሠላም ጓዱ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ በአገር ላይ የተቃጣውን የህልውና አደጋ ለመመከት የሚያስችል ስራ ይሰራል ብለዋል።
ለዚህም በውስጥም ሆነ በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ አንድነቱ እንዲጠናክር የሠላም ጓዱ የበኩሉን ይወጣል።
በሠላም አደፍራሾች የተጫሩ የውስጥ ግጭቶች በባሕላዊና አገራዊ እሴቶች እንዲፈቱ የሚሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
የሠላም ጓዱ በኢትዮጵያ በግጭቶች ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን ተዘዋውሮ መጎብኘቱን ፕሮፌሰር ብሩክ ገልጸዋል።
በዚህም በኮንሶ ጋላቦ እን በዳራሼ ጋቶ መጠለያዎች እንዲሁም በአጣዬ አካባቢ አልማ ቢሮ የተጠለሉትን ተፋናቃዮች መጎብኘታቸውን ጠቅሰዋል።
የጉብኝቱ ዓላማ ከተፈናቃዮች ጋር ተያይዞ ለዳያስፖራው ማኅበረሰብም ሆነ ለተቀረው ዓለም መሬት ላይ ያለውን እውነታ ለማሳወቅ ነው ብለዋል።
የሠላም ጓዱ በአገር ውስጥ ከሚገኙ ከተለያዩ ተቋማት ጋር ለመስራት መስማማቱንም ፕሮፌሰር ብሩክ ጠቁመዋል።