ለወሳኝ ኩነት ምዝገባ አዳዲስ ስልቶችን በመንደፍ የዜጎችን የተደራጀ መረጃ ለመያዝ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
ለወሳኝ ኩነት ምዝገባ አዳዲስ ስልቶችን በመንደፍ የዜጎችን የተደራጀ መረጃ ለመያዝ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል
አዲስ አበባ፣ ነሃሴ04/2013 (ኢዜአ) ለወሳኝ ኩነት ምዝገባ አዳዲስ ስልቶችን በመንደፍ "የዜጎችን የተደራጀ መረጃ ለመያዝ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል" ሲሉ የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ከሚል ተናገሩ።
ወይዘሮ ሙፈሪያት ይህን ያሉት "ሁሉም ሰው የሚታወቅበት ኢትዮጵያን በጋራ እንገንባ" በሚል መሪ ሃሳብ ለአራተኛው የወሳኝ ኩነት ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ በአዲስ አበባ እየተከበረ ባለበት ወቅት ነው።
በዚህ ወቅት ወይዘሮ ሙፈሪያት እንዳሉት፤ ለወሳኝ ኩነት አስፈላጊ የሆኑ የዜጎችን የተደራጀ መረጃ ለመያዝ መንግስት አሰራሮችን ሲያደራጅ ቆይቷል።
በዚህም ባለፉት ዓመታት ለልደት፣ ጋብቻ፣ ፍቺ እና የሞት የወሳኝ ኩነት ምዝገባ አበረታች ውጤት መመዝገቡን አመልክተው፤ አሁንም ጠንካራ ስራ እንደሚያስፈልግ በአጽንኖት ገልጸዋል።
ለዚህም አዳዲስ ስልቶችን በመንደፍ የዜጎችን መረጃ በተደራጀ መንገድ መያዝ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ለዚህም የሃይማኖት ተቋማት፣ ህብረተሰቡ፣ የክልልና የፌዴራል አመራር አባላት ርብርብ እንዲያደርጉ ጠይቀው፤ መንግስት በዜጎች መረጃ ላይ የተመሰረተ ሁሉን አቀፍ አገልግሎት ለማቅረብ እንደሚያስችለው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙጂብ ጀማል በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነጻጸር የወሳኝ ኩነት መረጃ አያያዝ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በቀረጸችው የ10 ዓመት ስትራቴጅ እቅድ ላይ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ መቶ በመቶ ለማድረስ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ሁሉም ርብርብ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
የወሳኝ ኩነት ምዝገባ በ1935 ዓ.ም አገልግሎት መስጠት የጀመረው ለውጭ አገራት መሆኑን ይታወሳል።