ህዝብን ደጀን ያደረገው የመከላከያ ሠራዊት የአገር ሉዓላዊነትን በአስተማማኝነት ያስጠብቃል- የምስራቅ ዕዝ መኮንኖች - ኢዜአ አማርኛ
ህዝብን ደጀን ያደረገው የመከላከያ ሠራዊት የአገር ሉዓላዊነትን በአስተማማኝነት ያስጠብቃል- የምስራቅ ዕዝ መኮንኖች
ድሬዳዋ ነሐሴ 3/2013 /ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ሕዝብን ደጀን ያደረገው የአገር መከላከያ ሠራዊት የአገርን ሉዓላዊነትን በአስተማማኝ ሁኔታ እንደሚያስከብር የምስራቅ ዕዝ ወታደራዊ መኮንኖች ያረጋግጣሉ።
በዕዙ የድሬዳዋ ደረጃ አንድ የመከላከያ ሪፈራል ሆስፒታል መኮንኖች ዛሬ በድሬዳዋ ችግኞች በተከሉበት ወቅት እንደለጹት ዕዙ የአገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ናቸው፡፡
ከመኮንንኖቹ ሌተና ኮሎኔል ተፈራ ማርቆስ እንዳሉት ለሰራዊቱ ልዩ ክብር ያለውን ህዝብ ደጀን ያደረገውን የህውሀት ሽፍታ ለመደምሰስ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
''ዛሬ እዚህ ሆስፒታል ላይ ችግኝ በመትከል የተሣተፍነው ሠራዊቱና ህዝቡ አንድነቱ በሁሉም መስክ የጠነከረና አገርን ለማሻገር የፀና መሆኑን ለማሳወቅ ነው'' ብለዋል፡፡
አገርን የሚያፈርሰው ጠላት ብቻ አይደለም የተፈጥሮ አደጋ ጭምር መሆኑንና በ1998 የድሬዳዋ ጎርፍ ትልቁ መማሪያ ነው ያሉት ደግሞ ሻለቃ ዶክተር ዩሱፍ አህመድ ናቸው፡፡
አሸባሪው ቡድን ለሰላም የተሰጠውን ዕድል በመግፋት አገርን ለማጥፋት የሚያደርገው እንቅስቃሴ ትውልዶች ለአገር ልዕልና የከፈሉትን መስዋዕትነት መናቅ ነው ብለዋል፡፡
ቡድኑን ለህግ ለማቅረብና የአገርን ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ በተጠንቀቅ ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
ሌላው ሻለቃ ራህማቶ ሂርጶ ''በጉልበቱ፣ በዕውቀቱ፣በገንዘቡ፣ በሞራልና በአካል ከሠራዊቱ ጎን ሁሌም የሚቆም ህዝብ ያለው ሠራዊት የትኛውንም የውጭ ጠላትን ለማሳፈርና የአገርን ልዕልና ለማረጋገጥ ለሰኮንድ አይተኛም''በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ሠራዊቱ የአገርን ልማትና አንድነት ለማረጋገጥ በሁሉም ቦታና ጊዜ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
የአገር ፍቅር ያለውና አንድነቷን ለማስጠበቅ ድጋፍ የሚያደርግ ሕዝብ ከጎኑ ያሰለፈ ሠራዊት ማንኛውንም ተልዕኮ ስኬት እንደሚያጠናቅቅ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡