የሀገርን ደህንነት ለሚጠብቀው መከላከያ ሰራዊት ድጋፋችንን እናጠናክራለን - ኢዜአ አማርኛ
የሀገርን ደህንነት ለሚጠብቀው መከላከያ ሰራዊት ድጋፋችንን እናጠናክራለን
ጅማ ነሐሴ 3/2013 /ኢዜአ/ በጅማ ከተማ የሚገኙት የኢትዮጵያ ቪዥነሪ አብያተ ክርስቲያናት ህብረት የወንጌል አማኞች ሃገርን ከአሸባሪው ህወሃት ለማዳን ውድ ህይወቱን ለሚከፍለው የሃገር መከላከያ ሰራዊት ደም ከመለገስ ጀምሮ በሁሉም ዘርፍ ከጎኑ ነን ይላሉ።
በከተማው በተመቻቸላቸው እድል ደማቸውን ለመከላከያው ከለገሱት መካከል ሜሮን እንዳሻው እንዳለችው ከመከላከያው ጎን ለመቆም ያላትን ፍላጎት ለማሳየት ያደረገችው መሆኑን ገልጻለች።
የሀገርን ደህንነት ለመጠበቅ ለቆመው መከላከያ ሁሉም የበኩሉን መወጣት ይኖርበታል ብላለች።
አቶ ታምራት ከበደ በበኩላቸው ለጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ሲሉ ለመጀመርያ ጊዜ ደም መለገሳቸውን ገልጸው፤ ደምን በመለገስ መከላከያውን በመታደግ ሀገርን የማዳን ዘመቻው አካል መሆናቸውን ገልጸዋል።
የቪዥነሪ አብያተ ክርስትያናት ህብረት የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ተወካይና የተገለጠ የእምነት ቃል ቸርች መስራች ፓስተር ጥላሁን መንግሥቱ እንደገለጹት የወንጌል አማኞች ህብረቱ ለሁለተኛ ጊዜ ደም በመለገስ ለመከላከያ ሰራዊቱ ያላቸውን አብሮነት እየገለጸ መሆኑን ተናግረዋል።
ፓስተር ጥላሁን አክለውም በቃሉ መሰረት "የምድር ጨውና የአለም ብርሃን ናችሁ" እንዳለው ሰውን ለማዳን ደማችንን አየለገስን ነው ብለዋል።
በሀገራችን የተፈጠረው ጦርነት ረግቦ ወደ ሰላም መምጣት እንዲቻልም ሁሉም አካላት ማሰብና መስራት አለባቸው ብለዋል ፖስተር ጥላሁን።
የጅማ ከተማ ጤና ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ኢንዲያ መሀመድ የእምነት ተቋማቱ አባላት በደም ልገሳ መርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው መከላከያውን ለመደገፍ ያደረጉት መነሳሳት የሚደነቅ ነው ብለዋል።
ሀገራችንን ከገባችበት የህልውና ጦርነት መመከት የምንችለው ሁላችንም በያለንበት በምንችለው ሁሉ ስንተባበር ነውም ብለዋል።
የጅማ ከተማ ደም ባንክ አስተባባሪ አቶ ሀይደር ኡመር በበኩላቸው የወንጌል አማኞች ህብረት ከዚህ በፊትም ደም የለገሱ መሆኑን አውስተው ዛሬም አንድ መቶ ዩኒት ደም መለገስ ችለዋል ብለዋል።
የጅማ ከተማ ህብረተሰብም ደም በመለገስ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ በጎ ፍቃደኛ ህዝብ አንደሆም አቶ ሀይደር ተናግረዋል ።