ቀጥታ፡

በምርጫው ተፎካክረን ኢትዮጵያ አሸንፋለች፤ አገር ለማዳን ሳንፎካከር በጋራ ቆመን እንመክታለን

ነሐሴ 03 / 2013 (ኢዜአ) በምርጫው ተፎካክረን ኢትዮጵያ አሸንፋለች፤ አገር ለማዳን ሳንፎካከር በጋራ ቆመን እንመክታለን ሲሉ የተፎካካሪ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እና የእናት ፓርቲ ከፍተኛ ኃላፊዎች በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት በ6ኛው አጠቃላይ ምርጫ የነበረው ፉክክር ኢትዮጵያን አሸናፊ አድርጓል።

ኢትዮጵያን አሁን ለገጠማት የህልውና አደጋ ደግሞ ውድድርና ፉክክር ሳይሆን በምክክር ጠላትን መመከት መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም የየፓርቲያቸው አመራሮችና ደጋፊዎች አገር ለማዳን በጋራ በመቆም ለመመከት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የእናት ፓርቲ ዋና ጸሐፊ አቶ ጌትነት ወርቁ፤ በስድስተኛውን አጠቃላይ ምርጫ ፓርቲያቸው አገርና ህዝብን በማስቀደም ለምርጫው ሰላማዊነት መስራቱን አስታውሰዋል።

በመሆኑም በቅድመ-ምርጫ፣ በምርጫና በድህረ-ምርጫ የጎላ ችግር አለመከሰቱ እንደ አገር መልካም የዴሞክራሲ ጅማሮ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም በድህረ-ምርጫ ከምርጫው ጋር በተገናኘ የተከሰተ ችግር አለመኖሩን ህዝቡና የፖለቲካ ፓርቲዎች ትልቁን ድርሻ እንደሚወስዱ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ሰላም፣ ቀጣይነት፣ አንድነትና ሉዓላዊነት መከበር ሁሌም በአንድ የሚቆሙ መሆናቸው አገር በችግር ውስጥ ሆና በአንድ ሐሳብ ምርጫውን በሰላም ማለፍ መቻሉን ነው ያስረዱት።

በአጠቃላይ ምርጫው የኢትዮጵያ ጉዳይ በመሆኑ በሰላም ተጠናቆ አገር እንድታሸንፍ በጋራ መሰራቱ "በሰላም በመጠናቀቁ ብቻ ኢትዮጵያ አሸንፋለች!" ብለዋል።

የተከናወነው ምርጫ ለአፍሪካውያን ትምህርት ለቀጣይ ትውልድ ደግሞ የሚጠቀስ ታሪክ ጥሎ ያለፈ መሆኑን አስረድተዋል።

ከፖለቲካና ምርጫ በላይ ኢትዮጵያን በማስቀደም አሁን የገጠማትን ችግር ለመመከት ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያን አሁን ለገጠማት የህልውና አደጋ ደግሞ ከመንግሥት ጎን በመሆን አስፈላጊውን ሁሉ እገዛና ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።

ባልተገባ መንገድ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ሊያሳድሩ የሚሞክሩ ኃይሎችም ተቀባይነት የላቸውም ነው ያሉት።  

እናት ፓርቲ ከምርጫ ጋር በተገናኘ 253 ቅሬታዎችን ለምርጫ ቦርድ ያቀረበ ሲሆን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት በማድረግ አገርን በማስቀደም ለአገር ሰላምና አንድነት አየሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የኢዜማ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ፤ በኢትዮጵያ የተደረገው ምርጫ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የተሳተፉበትና በተቻለ አቅም ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ የተሞከረ መሆኑን አውስተዋል።

ከምርጫው ጋር ተያይዞ ሁከትና የሰላም እጦት ይከሰታል የሚል ስጋት በተለያዩ አካላት ዘንድ የነበረ ቢሆንም የጎላ ችግር ሳይከሰት መጠናቀቁን ገልጸዋል።

"ምርጫውን የምናደርገው ለራሳችን ስንል ነው፤ ለሌላ ሦስተኛ ወገን ስንል አይደለም" ያሉት አቶ ናትናኤል ሌሎች አካላት ምርጫው ላይ የሚወስዱት አቋምና የሚሰጡት ግምገማ እንደማያሳስብ ተናግረዋል።

ኢዜማ ከቅድመ-ምርጫ ጀምሮ ያጋጠሙትን ችግሮች ለሚመለከተው አካል አቅርቦ አጥጋቢ መልስ ያላገኘባቸውን ለጠቅላይ ፍርድ ቤት በማቅረብ እየተከታተለ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በቀጣይ በህዝብ ድምጽ ያሸነፈው ብልጽግና ፓርቲ መንግሥት ሲመሰርት በማህበራዊ፣ በምጣኔ ሃብትና ፖለቲካ እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት በጋራ አገራቸውን ለማበልጸግ ዝግጁ መሆናቸውን ፓርቲዎቹ ገልጸዋል።

በምርጫው ተፎካክረን ኢትዮጵያ አሸንፋለች፤ አገር ለማዳን ሳንፎካከር በጋራ ቆመን ጠላቶችን እንመክታለን ሲሉ የፓርቲዎቹ አመራሮች አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም