አሸባሪው ትህነግ ኢትዮጵያዊያን በጋራ የተነሱበትን ሃገር የማዳን ትግል በሃሰተኛ መረጃ ማሸነፍ አይችልም - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ትህነግ ኢትዮጵያዊያን በጋራ የተነሱበትን ሃገር የማዳን ትግል በሃሰተኛ መረጃ ማሸነፍ አይችልም
ደሴ ነሐሴ 3/2013 /ኢዜአ / አሸባሪው ትህነግ በጦር መሣሪያም ሆነ በሃሰተኛ መረጃ የስነ-ልቦና ጦርነቱ መላው ኢትዮጵያዊያን በአንድነት የተነሱበትን ሃገራዊ የተቃውሞ ትግል ማሸነፍ የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል።
ሐሰተኛ ወሬ የሚያደርሰው የሥነ ልቡና ጫና በመከላከል ላይ ባተኮረውና በደሴ ከተማ በተካሔደ ውይይት ላይ የተገኙት በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሳይኮሎጂ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር አውጋቸው ሽመልስ እንደተናገሩት አሸባሪው ቡድን በከፈተው ጦርነትና እያሰራጨ ባለው የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ምኞቱን ማሳካት አይችልም::
ረዳት ፕሮፌሰሩ አውጋቸው ትህነግ ሥልጣኑን ለማራዘም የፖለቲካ ሴራዎች ሲፈጽም የኖረና የሐሰት ወሬ በመፍጠር የተካነ ድርጅት መሆኑን ይገልጻሉ።
በተለይ የአማራን ሕዝብ ጠላት በማድረግ ጅምላ ጭፍጨፋ፣ አፈናና ዘረፋ ከመፈፀሙም ባለፈ የሐሰት የታሪክ ትርክት በመፍጠር ጭምር የሥነ ልቡና ጫና ሲያደርስ መቆየቱንም ተናግረዋል።
“አሁንም እየፈፀመ ካለው በደል ባለፈ በተለመደው የውሸት ፕሮፓጋንዳው የሕዝቡ ሥነ ልቡና ለመጉዳት የሚያርገውን ጥረት መመከት ያስፈልጋል” ብለዋል።
“አሸባሪው ቡድን ዋና ኃይሉ ውሸትና ፕሮፓጋንዳ ነው” ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር አውጋቸው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነቱን ማጠናከርና ለአገር መከላከያ ሠራዊት የሚያደርገውን ድጋፍ ማጠናከር ትህነግን ለመደምሰስ አስፍላጊ መሆኑን ጠቁዋል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ሰላምና የሕዝብ ደህንነት ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ሐሰን መሐመድ በበኩላቸው አሸባሪው ቡድን የሚያደርሰውን ሁለንተናዊ ጫና ለመመከት በተደራጀ አግባብ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ቡድኑ አማራን አዳክሞ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የሚያርገውን ሴራ ለማክሸፍ ከአጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ህብረተሰቡ የአካባቢውን ሰላም ከመጠበቅ ባሻገር፤የሐሰት ፕሮፓጋንዳውን እንዲመክትም አሳስበዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊ ወጣት አዩብ ሰይድ አሸባሪው ቡድን በህዝቡ ላይ የስነ ልቦና ጫና በመፍጠርና በማደናገር እንዲሰደድና እንዲፈናቀል የሚያደርገው ጥረት እንደማይሳካለት ገልጿል፡፡
''ተደራጅተን አካባብያችንን ከመጠበቅ ባለፈ ግንባር ዘምተን አይቀጡ ቅጣት በመቅጣትና መቅበር ኃላፊነታችንን ለመወጣትም ዝግጁ ነን'' ብሏል፡፡
ወጣት ህይወት በለጠ በበኩሏ አሸባሪው ቡድን ህልውናውን እንዲያስቀጥል ዕድል መስጠት እንደማይገባ ገልጻ፣ “ትህነግን ተባብረን መቅበርና ኢትዮጵያን ነጻ መውጣት ይኖርብናል” ብላለች።
ቡድኑን ለመደምሰስ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኗንም አስታውቃለች፡፡
ዛሬ በደሴ ከተማ በተካሔደው ውይይት ላይ የአማራ ክልልና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች፤ ወጣቶችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡
አሸባሪው ህወሃት በፎቶግራፍ ቅንብር፣ በሃሰተኛ ተንቀሳቃሽ ምስል ሌሎች መረጃዎቹ የውስጥና የውጭ ደጋፊ ተከፋዮቹን በማስተባበር የህዝብን ሰላም ማወክ የሚታወቅበት የዘወትር ተግባሩ እንደሆነ በተለያዩ አካላት ሲጋለጥ መቆየቱ ይታወቃል።