በኢትዮጵያ የምርምርና ጥናት ስራዎች ለፖሊሲ ግብአት እየሆኑ አይደለም - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የምርምርና ጥናት ስራዎች ለፖሊሲ ግብአት እየሆኑ አይደለም
ነሐሴ 3/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የምርምርና ጥናት ስራዎች በብዛት ለፖሊሲ ግብአት አለመሆናቸውን የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ገለጸ።
በተመራማሪዎችና በፖሊሲ አውጪዎች መካከል ያለውን ክፍተትን መለየትና መፍትሔን ማበጀት ዓላማ ያደረገና የዘርፉን ሙሁራን ያሳተፈ ስልጠና በአዲስ አበባ ተጀምሯል።
የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጽጌ ገብረማሪያም፤ በመርሃ ግበሩ ማስጀመሪያ ላይ እንደተናገሩት በብዛት እየተተገበሩ የሚገኙት ፖሊሲዎች ብዙ ዓመታትን ያስቆጠሩ ናቸው።
በኢትዮጵያ የምርምርና ጥናት ስራዎች በብዛት ለፖሊሲ ግብአት ባለመሆናቸው አሁናዊ ሁኔታዎችን በማነጻጸር እየተሻሻሉና ማስተካከያ እየተደረገባቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ችግሩ በተመራማሪዎችና በፖሊሲ አውጪዎች መካከል መናበብ ባለመኖሩ የተፈጠረ መሆኑን የአካዳሚው ፕሬዝዳንት ገልጸዋል።
በመሆኑም በቀጣይ በፖሊሲ የሚመሩ ጉዳዮች ላይ በማተኮር አንጋፋና ወጣት ተመራማሪዎች ጥናቶችን እንዲያከናውኑና ግብአት እንዲሆኑም ማድረግ ይገባል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ፖሊሲዎች ሲዘጋጁም ሆነ ሲሻሻሉ ከምርምር ውጤቶች ጋር እንዲተሳሰሩ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ለዚህም አካዳሚው ትልልቅና አገራዊ ጉዳዮች ናቸው ብሎ በለያቸው አበይት ጉዳዮች ዙሪያ ለጥናት አድራጊዎችና ተመራማሪዎች ስልጠና መስጠት አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል።
በዛሬው እለት የተጀመረው ስልጠናም ምርምሮችን ለፖሊሲ ግብአት እንደት ማዋል እንደሚቻል ግንዛቤ የሚፈጥር መሆኑን ፕሮፌሰር ጽጌ ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የስነ-ህዝብ ትምህርት ማዕከል አባልና የፕላንና ልማት ኮሚሽን አማካሪ ዶክተር ተረፈ ደገፋ የህዝብ ቁጥር ብዛትና ያለው የሃብት ምጣኔ ባለመጣጣሙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር እየተፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል።።
በዚህም ዜጎች ለከፋ የኑሮ ችግር ከመጋለጣቸው ባሻገር የአገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም ደካማ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የአሰራር ለውጦች፣ የፖሊሲ ዝግጅትና ማሻሻያዎች ቢደረጉም እስካሁን አመርቂ ውጤቶች እየተመዘገቡ አይደለም ብለዋል።
በመሆኑም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በተለይ ምሁራን የሌሎች አገራትንም ተሞክሮ በመቀመር በዘርፉ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
ለዚህም መንግስታዊ ተቋማትና የሚመለከታቸው አካላት ቅንጅታዊ አሰራር መፍጠር አለባቸው ብለዋል ዶክተር ተረፈ።
በስልጠናው የአካዳሚው አባላት ወጣትና ነባር ተመራማሪዎች የተሳተፉ ሲሆን ዛሬን ጨምሮ ለተከታታይ አምስት ቀናት የሚቆይ ይሆናል።