በኢትዮጵያና እስራኤል መካከል የቆየው ጠንካራ ታሪካዊ እና መንፈሳዊ ትስስር የንግድና ኢንቨስትመንት ለማጠናከር ምቹ አጋጣሚ ይፈጥራል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያና እስራኤል መካከል የቆየው ጠንካራ ታሪካዊ እና መንፈሳዊ ትስስር የንግድና ኢንቨስትመንት ለማጠናከር ምቹ አጋጣሚ ይፈጥራል
ነሃሴ 3/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያና በእስራኤል መካከል የቆየው ጠንካራ እና መንፈሳዊ ትስስር በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ለማጠናከር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተገለፀ፡፡
የኢትዮጵያ ኢምባሲ ከእስራኤል የላኪዎች እና ዓለም አቀፍ ንግድ ትብብር ተቋም ጋር በመተባበር በእስራኤል እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የኢንቨስትመንት እና የንግድ ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ምክክር አድርገዋል፡፡
በምክክር መድረኩ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያደረጉ ባለሃብቶች፣ በኢትዮጵያ በግል ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው አዳዲስ ኩባንያዎች ባለቤቶችና አመራሮች ተገኝተዋል፡፡
የተቋሙ ምክትል ኃላፊ ሳቢን ሴጋል በተለያዩ የኢንቨስትመንት እና የንግድ ዘርፎች የተሰማሩ ባለሃብቶች በሥራቸው ዙሪያ የሚያነሷቸውን ችግሮች በጋራ ለመፍታት እንደዚህ አይነት መድረክ መዘጋጀቱ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ትብብር ከፍ ለማድረግ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው በመጠቆም ለሁሉም ምስጋና አቅርበዋል።
በእስራኤል የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. አምባሳደር ረታ ዓለሙ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት፣ ንግድና የቱሪዝም አማራጮችን በሚመለከት ሰፊ ገለጻ አቅርበዋል።
በማያያዝም ኢትዮጵያ እና እስራኤል ጠንካራ ታሪካዊ እና መንፈሳዊ ትስስር ያላቸው መሆኑን አስታውሰው፤ ይህ ትስስር በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ለማጠናከር ምቹ አጋጣሚ መሆኑን አስረድተዋል።
የተቋሙ የዓለም አቀፍ የቢዝነስ ጉዳዮች ኃላፊ ሚስ ሳቢን ሴጋል በበኩላቸው በእስራኤል እና በኢትዮጵያ መካከል የሚደረገው የኢኮኖሚ ትብብር ከፍተኛ መሻሻልን እያሳየ መሆኑን በመጥቀስ፣ ይህ ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል በጋራ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በተጨማሪም በባለሃብቶቹ የሚነሱ ችግሮችን በጋራ መፍትሄ በመስጠት፣ ኢትዮጵያ ያላትን ምቹ የቢዝነስ ዕድሎች መጠቀም እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በአገራችን ኢንቨስት ያደረጉ ባለሃብቶች በበኩላቸው ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ የኢንቨስትመንት አማራጮች ያሏት መሆኑን በማንሳት፣ በጀመሩት ሥራ ውጤታማ መሆናቸውን ጠቅሰው በአንዳንድ ምክንያቶች እየገጠማቸው ያለውን ተግዳሮት አስረድተዋል።
በተለይ አላስፈላጊ በሆኑ የቢሮክራሲ ሂደቶች የተነሳ የተጀመሩት ሥራዎች በፈለጉት ፍጥነት እየሄዱላቸው አለመሆኑና መስተጓጎል እንደፈጠረባቸው አስታውቀዋል።
አምባሳደር ረታ መንግስት በኢንቨስተሮች የሚነሱ ችግችን ለመፍታት በመዋቅር በሕግ እና በአስራር ሁኔታዎችን ለማሻሻል የወሰዳቸውን እርምጃዎች በማስረዳት መፍትሄ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ ከምን ጊዜውም በተለየ ሁኔታ በርካታ የኢኮኖሚና የሕግ ማሻሻያዎች የተደረጉ መሆኑን፣ በተለይ ትኩረት በተሰጣቸው ዘርፎች ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው የውጭ ባለሃብቶችን ለማበረታታትና አሠራሩን የተሻለ ለማድረግ የወጡትን ሕጎች በማስረጃነት በመጥቀስ ኢምባሲያችን ችግሮቹን ለመቅረፍ በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አስረድተዋል።
በማያያዝም ከኤምባሲው የትኩረት አቅጣጫዎች አንዱ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ትብብር ማሳደግ መሆኑን ገልጸው፣ ይህንንም ተፈጻሚ ለማድረግ ኤምባሲው የተጣለበትን ኃላፊነት እየተወጣ መሆኑን አስረድተዋል።