ቀጥታ፡

ኤጀንሲው ከ27 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገዙ የሕክምና ቁሳቁሶችን ለጤና ተቋማት ማሰራጨቱን አስታወቀ

አርባ ምንጭ ነሀሴ 2/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መድሐኒት አቅራቢ ኤጀንሲ በ2013 በጀት ዓመት ከ27 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ከውጭ ሀገር የተገዙ የተለያዩ የሕክምና ቁሳቁሶችን ለጤና ተቋማት ማሰራጨቱን አስታወቀ።

ኤጀንሲው ለጤና ተቋማት ካቀረባቸው መድሃኒቶች ሽያጭ ያልተከፈለው ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ እንዳለውም ገልጿል።

የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ 4ኛው የአቅርቦት ሰንሰለት ጉባዔ  በአርባ  ምንጭ  ከተማ እየተካሄደ ነው።

በጉባኤው ላይ የኤጀንሲው  ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ  እንዳሉት  ጤንነቱ የተጠበቀ ዜጋ በመፍጠር የሀገሪቱን ዕድገት ለማረጋገጥ የጤና ግብአት አቅርቦት ወሳኝ ሚና አለው።

ይህን እውን ለማድረግ በሀገሪቱ የጤና አገልግሎት ሥርአትን ለማሳለጥና  ጠንካራ  የግብዓት አቅርቦት ሠንሰለት ለመዘርጋት እየተሰራ  መሆኑን ተናግረዋል።

ሆኖም ከኮቭድ-19 ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ በአገር ውስጥና በውጭ አገራት የአቅርቦት ሰንሰለት መቀዛቀዝ፣ የመድሃኒት ዋጋ መናርና  የበጀት  እጥረት  የኤጀንሲውን  ተግባር  መፈታተኑን  አመልክተዋል።

"ችግሩን በመቋቋም ለጤና ተቋማት በሚያስፈልጉ የመድሃኒቶች፣ የሕክምና መገልገያ  መሳሪያዎችና ኬሚካል አቅርቦት ሥራ ላይ የተሻለ አፈጻጸም ታይቷል" ብለዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ በ2013 በጀት ዓመት ከ27 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ  የተለያዩ  የሕክምና ቁሶች ተገዝተው ለጤና ተቋማት ተሰራጭተዋል።

በዚህ ዓመት ከውጭ የሚገቡ መድሃኒቶች ወደብ ላይ የሚኖራቸውን የ94 ቀን ቆይታ ወደ 7 ቀን ዝቅ ማድረግ መቻሉን የገለጹት ደግሞ በኤጀንሲው የፕላን  ክትትልና ግምገማ  ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ፀጋ ናቸው።

በእዚህም ለመጋዘንና ለተለያዩ ወጪዎች ይወጣ የነበረውን 58 ሚሊዮን ብር ማዳን መቻሉን ነው ያመለከቱት።

ለዓመታት በመጋዘን ተከማችተው የነበሩና ግምታቸው 1ቢሊዮን 700 ሚሊዮን ብር  የሆነ የሕክምና ቁሶችን ለጤና ተቋማት በማሰራጨት በአቅርቦት ላይ የነበረውን እጥረት ለማቃለል መሰራቱንም አክለዋል።

ኤጀንሲው ለጤና ተቋማት በሽያጭ ላቀረባቸው መድሃኒቶች ተቋማቱ በወቅቱ ክፍያ እየፈጸሙ እንዳልሆነ የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ በእዚህ ምክንያት ከ1 ቢሊዮን 100  ሚሊዮን  ብር  በላይ ገንዘብ በጤና ተቋማት እጅ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ይህም በኤጀንሲው ሥራ ላይ ጫና እያሳደረ መሆኑን ነው የገለጹት።

ለሁለት ቀናት እየተካሄደ ባለው ጉባዔ የ2013 በጀት ዓመት ዕቅድ  ክንውን  እንደሚገመገም ለማወቅ ተችሏል'

በመድርኩም ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የዘርፉ የሥራ ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም