ቀጥታ፡

"ለሠራዊቱ ከተረፈን ሣይሆን ካለን ላይ እንሰጣለን፤ በአካል ግንባር ድረስ ለመዝመትም ዝግጁ ነን" --እናቶች

ድሬዳዋ፣ ነሐሴ 2/2013(ኢዜአ) ለሀገር አንድነትና ሉአላዊነት መከበር መስዋዕት እየከፈለ ላለው መከላከያ ሠራዊትና ልዩ ኃይል ከተረፈን ሳይሆን ካለን ላይ በመስጠት አገርን ለማሻገር እንደሚሰሩ  ኢዜአ ያነጋገራቸው የድሬዳዋ እናቶች ገለጹ።

በድሬዳዋ የቀበሌ 02 እናቶች ዛሬ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ  የሚሆን  ስንቅ በማዘጋጀት ሥራ ተጠምደዋል።

የድሬዳዋን ዕድገት የናደውንና ህዝቧን ለድህነት የዳረገው የትህነግ የሽብር ቡድን  ለህግ እንዲቀርብ ስንቅ ከማዘጋጀት ባለፈ ግንባር ድረስ በመሄድ ለመፋለም ዝግጁ መሆናቸውንም ነው የገለጹት።

የድሬዳዋ አስተዳደር ዘጠኝ የከተማና የገጠር ቀበሌዎች የህይወት መስዋዕትነት ጭምር  እየከፈለ ለሚገኘው መከላከያ ሠራዊት ደም በመለገስ፣ ገንዘብ በማዋጣትና ግንባር ድረስ በመዝመት አጋርነታቸው እያረጋገጡ ይገኛሉ፡፡

በዛሬ ዕለትም በድሬዳዋ ቀበሌ 02 የሚገኙ እናቶች በራሳቸው  ፍቃድና ተነሳሽነት  ግማሽ  ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ በማዋጣት ለሠራዊቱ ስንቅ እያዘጋጁ መሆኑናቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።

በስንቅ ዝግጅቱ ላይ እየተሳተፉ ካሉ እናቶች መከካል ወይዘሮ ውባየሁ ንጋቱ እንዳሉት  ሠራዊቱ አገርን ለማስከበርና ዳር ድንበሯን ለማረጋገጥ ህይወቱን እየሰጠ ነው።

"እኛም የሠራዊቱ ተልዕኮ ስኬታማ እንዲሆን ከተረፈን ሳይሆን ካለን በማዋጣት ስንቅ በማዘጋጀት ደጀንነታችንን እያረጋገጥን እንገኛለን" ብለዋል፡፡

"ህወሓት አገርን ለማስተዳደር ሳይሆን ለመከፋፈልና ለማፍረስ እንደመጣ አንዱ ማሳያ የድሬዳዋ 10ሺህ ቤተሰብ መተዳደሪያ የሆኑትን ምድር ባቡርና የድሬዳዋ ታሪካዊ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካን አፍርሶ መዝረፉ ዋና መገለጫ ነው"  ያሉት ደግሞ ወይዘሮ  አዘናጋሽ  ጎ ሣ  ናቸው፡፡

እሳቸው እንዳሉት የሰላምና የእፎይታ ጊዜን አልቀበል ያለውን ይህን ነቀርሳ በተቀናጀ መንገድ ለህግ ለማቅረብ የድሬዳዋ ሴቶች ምንግዜም ዝግጁ ናቸው፡፡

ህጻን ልጃቸውን አዝለው ለሠራዊቱ ስንቅ በማዘጋጀት ላይ የነበሩት ወይዘሮ አይሻ ሙመድ  በበኩላቸው ህጻናትን ለጦርነት እየማገደ ያለው የሽብር ቡድን ለህግ  እንዲቀርብ በጦር ሜዳ ዘምተው አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል  ዝግጁ  መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

"ለሠራዊታችን ደም በመለገስ፣ ገንዘብ በማዋጣትና ዛሬ ደግሞ ስንቅ በማዘጋጀት ተግባር ላይ መሰማራታችን አስደስቶናል" ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ንግስቴ መንገሻ የተባሉ እናት ናቸው፡፡

የ60 ዓመቷ ወይዘሮ ንግስቴ "ዕድል ከተሰጠኝ ነብሴን ለሠራዊቱ ለመስጠት፤ ከሠራዊቱ ጎን በመሆንም መስዋዕት ለመክፈል ተዘጋጅቺያለሁ" ሲሉ አክለዋል፡፡

ወይዘሮ ምስራቅ ሽበሺ በበኩላቸው ለሠራዊቱና ለልዩ ሀይሉ የተረፋቸውን ሣይሆን  ካላቸው ላይ  ለመስጠትና እስከ መጨረሻው ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን ነው የተናገሩት፡፡

አገራችንን ወደ ብልጽግና ለማሻገር የሚከናወኑ ተግባራትን  ዳር ለማድረስ  ለሠራዊቱ  ከስንቅ ዝግጅት ባሻገር የሽብር ቡድኑ ተላላኪዎችን ከፀጥታ አካላት ጋር  በመተባበር  ለህግ እያቀረቡ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ ሶፊያ አደም ናቸው፡፡

"ልጆቻችንን ግንባር ልከናል፤ እኛም ካስፈለግን ግንባር ድረስ እንሄዳለን" ብለዋል፡፡

በድሬዳዋ የቀበሌ 02 መስተዳድር ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ወንድምአገኝ በሻህ በየደረጃው የሚገኘው ህብረተሰብ ሠራዊቱ ተልዕኮውን እንዲያሳክ ድጋፍ እየደረገ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ከገንዘብ መዋጮና ከደም ልገሳ በተጨማሬ በዛሬው ዕለት በ22 መንደሮች  የሚገኙ  የድሬዳዋ ነዋሪዎች ግማሽ ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ገንዘብ ስንቅ እያዘጋጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አቶ ወንድምአገኝ እንዳሉት ሌሎቹም የድሬዳዋ ነዋሪዎች ተመሳሳይ  ድጋፍ  ለማድረግ  በዝግጅት ላይ ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም