ቀጥታ፡

ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት የሚከፈል መስዋዕትነት እየተከፈለ አገር ትቀጥላለች

አዲስ አበባ፣ነሃሴ 02/2013(ኢዜአ) ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት የሚከፈል መስዋዕትነት እየተከፈለ አገር እንደምትቀጥል በአዲስ አበባ ከተማ የመከላከያ ሠራዊቱን ለመደገፍ በተካሄደው ሰልፍ ላይ የታደሙ አስተያየት ሰጪዎች ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማና በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ነዋሪዎች በጋራ ከአገር መከላከያ ሠራዊት ጎን መሆናቸውን ያሳዩበት ሰልፍ ዛሬ በመስቀል አደባባይ  ተካሂዷል።

የሰልፉ ተሳታፊዎች እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ለዛሬ የበቃችው ልጆቿ ከጥንት ጀምሮ በከፈሉት መስዋዕትነት ነው።

የቅርብ ጊዜ የኢትዮጵያ ታሪክ እንኳን ቢቃኝ ኢትዮጵያዊያን ለሰላማቸውና ለአንድነታቸው ሲሉ በጋራ ተፋልመው ድል ተቀዳጅተዋል።

ዛሬም የኢትዮጵያን ሕልውናና አንድነት እየተፈታተነ የሚገኘውን የአሸባሪውን ሕወሓት ቡድን የአገሬው ሕዝብ በጋራ እየተፋለመ ይገኛል።

የጫንጮ ከተማ ነዋሪው አቶ ቦረና አገሪ ኢትዮጵያውያን ፈተና ሲገጥማቸው "አንድነታቸው ይጠነክራል እንጂ ላልቶ አያውቅም" ይላሉ።

በታሪክ እንደሚታወቀው በአገር ጉዳይ የኢትዮጵያን ሕዝብ መከፋፈል እንደማይቻል የተናገሩት አቶ ቦረና፤ ''አሁንም የድል ታሪካችን ይደገማል'' በማለት ተስፋቸውን ገልጸዋል።

አሸባሪው ሕወሓትን እስከመጨረሻው ለማጥፋትና ከጦርነት አዙሪት ለመውጣትም በሚችሉት ሁሉ ከአገር መከላከያ ሠራዊት ጎን እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

ሌላው የሱሉልታ ከተማ ነዋሪ አቶ ሐብታሙ ዋቅጅራ እንደሚናገሩት፤ አሸባሪው ሕወሓትን በዘላቂነት ለማስወገድ አሁንም ኢትዮጵያውያን በአንድነት 'ከዳር እስከ ዳር' መነሳት አለባቸው።

አሸባሪው ቡድን የምን ጊዜም የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት መሆኑን ያስታወሱት አቶ ሐብታሙ፤ ''ሕዝቡ እንደ አባቶቹ መስዋዕትነት ከፍሎ ቡድኑን ሊያስወግደው ይገባል'' ብለዋል።

"አሸባሪው ቡድን በቀጣይ የኢትዮጵያውያን ስጋት እንዳይሆን ሁሉም ተባብሮ ፍጻሜውን ማግኘት አለበት" የሚሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ነዋሪው አቶ ካሣሁን ወርቃየሁ ናቸው።

"አሸባሪውን አስወግደን በሰላም ወጥተን የምንገባበት፤ ልጆቻችንን ያለ ስጋት እንዲኖሩና ወደ ልማት በሙሉ አቅም መግባት የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት አስፈላጊ ነው" ይላሉ። 

ኢትዮጵያ ከገባችበት ችግር መውጣት የምትችለው በራሷ ዜጎች ትግልና ጥረት እንደሆነ የሚናገሩት ሌላው የአዲስ አበባ ነዋሪ አቶ በቀለ ባይሳ ናቸው።

የጥንት የኢትዮጵያ ታሪክ የሚያስረዳው ኢትዮጵዊያን ችግር ሲገጥማቸው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ችግራቸውን ሲፈቱና ከገጠማቸው ፈተና በድል ሲወጡ መሆኑንም አብራርተዋል።

በኦሮሚያ ክልል አደአ በርጋ ወረዳ ነዋሪው ወጣት ኃይሉ ታደሰ በበኩሉ፤ በሁሉም ነገር ከአገር መከላከያ ሠራዊት ጎን መሆኑን ገልጿል።

ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለአገር አንድነትና ሰላም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን ጠቁሞ፤ ለዚህም ምንም ጥርጣሬ እንደሌለው ተናግሯል።

ሰላማዊ ሰልፉ"ኢትዮጵያን ለማዳን እዘምታለሁ! የትም! በምንም! " በሚል መሪ ሀሳብ በመስቀል አደባባይ ተካሂዷል።

ሌሎች በርካታ መልዕክቶችም የተላለፉበት ሲሆን፤ ከአዲስ አበባ ዙሪያ የመጡ ሰልፈኞች ባሳዩት የፈረስ ትርዒት ኩነቱን አድምቀውት አርፍደዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም