ቀጥታ፡

አሸባሪው ህወሃት የከፈተውን ጦርነት ለመከላከል በቁርጠኝነት ተነስተናል --የደብረማርቆስ ወጣቶች

ደብረ ማርቆስ፣ነሐሴ 2 /2013 (ኢዜአ)አሸባሪው የህወሃት ጁንታ የከፈተውን ጦርነት ለመከላከል በቁርጠኝነት ተነስተናል ይላሉ የደብረ ማርቆስ ወጣቶች።

የከተማው ወጣቶች አሸባሪውን ቡድን በተለይ በአማራ ክልል እያደረገ ያለውን መስፋፋት ለመግታት

ወታደራዊ ስልጠና መውሰዳቸውንም ይገልጻሉ።

በዚህም አካባቢያቸውን በንቃት በመጠበቅ የኢትዮጵያ አንድነት ለማፈራረስ የሚንቀሳቀሰውን የህወሃትን ሴራ እናከሽፈዋለን ይላሉ።

የከተማው ቀበሌ 07 ነዋሪ ወጣት ዘሪሁን ጥላሁን ጁንታው ሥልጣን ላይ  በነበረበት ዘመን  የአገር ሃብት ዘርፎ በውጭ በማከማቸቱ  ለሥራ ፈጠራ  የሚውል ሀብት  በማጣት  ወጣቱ ለስደት በመዳረግ ህይወቱንና አካሉን ማጣቱን ያስታውሳል።

በመከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት በመክፈትና አጎራባች ክልሎችን በመውረር የአገሪቱን ሰብዓዊና ቁሳዊ ሃብት እንዲወድም ማድረጋቸውንም  ገልጿል።

ስለሆነም አሸባሪው ቡድን የሌሎችን ሰላምና ደህንነት በማናጋት አገር ለማፍረስ የያዙት ሴራ ለማክሸፍ ወታደራዊና ሥነ ልቡናዊ ስልጠና ወስጄ አካባቢዬን በመጠባበቅ እገኛለሁ ብሏል።

"የክልሉ መንግሥት ትጥቅ ከሰጠኝ ግንባር ድረስ ሂጄ በመሰለፍ አሸባሪው ህወሃትን ፊት ለፊት ለመፋለም ቁርጠኛ ነኝ" ሲልም  አቋሙን አሳውቋል።

''ህወሃት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ካልተደመሰሰ ኢትዮጵያውያን ሰላም አናገኝም'' የሚለው ደግሞ በከተማዋ የ03 ቀበሌ ነዋሪው ወጣት ጊዜ ይልማ ነው።

ህወሃት በሥልጣን ላይ እያለ በንጹሃን ዜጎቻችን የፈጸመው ግፍና በደል ሳያንስ በአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት መፈጸሙና የአማራ ክልልን መውረሩ እንዳስቆጣው ይናገራል ።

በተለይም አሁን ላይ መንግሥት ያደረገውን የተናጠልተኩስ አቁም ውሳኔ አጋጣሚ በመጠቀም እያደረገ ያለው መስፋፋት ለመግታት ስልጠና ወስዶ ወደ ግንባር ለመዝመት ተዘጋጅቼያለሁ ብሏል።

ጥሪ እስኪደረግለትም ከተማውንና የአካባቢው ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ  ተግባር  ላይ  መሰማራቱን አስታውቋል።

የቀበሌ 05 ነዋሪዋ ወጣት ትዕግስት መርሻ በበኩሏ ወታደራዊ ስልጠና  ተከታትዬ   አሸባሪውን  ህወሃት ለመፋለም ጥሪ እየተጠባበቅኩ ነው ትላለች።

''ሰላም ከሌለ ትዳር መያዝ፣ ልጅ መውለድ እና ሰርቶ ማትረፍ አይገኝም''ያለችው ወጣቷ፣ አማራን ለማጥፋትና አገር ለመበተን ቆርጦ እየተንቀሳቀሰ በመሆኑ በቆፈረው ጉድጓድ ራሱን ለመቅበር መዘጋጀቷን ተናግራለች።

በአሁኑ ወቅትም ለአገር መከላከያ ሠራዊትና ለሌሎች ጸጥታ ኃይሎች ስንቅ  የሚሆኑ  የደረቅ ምግቦች ዝግጅት ላይ እየተሳተፈች መሆኑን ገልጻለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም